በአማሮ ልዩ ወረዳ እና በምዕራብ ጉጂ ዞን አዋሳኝ ቀበሌዎች በሚኖሩ ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ያለመ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሄደ

ሐሙስ ኀዳር 1 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ አጎራባች ቀበሌዎች እና በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን ሱሮ ባርጉዳና ገላና ወረዳዎች በሚኖሩ ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር በእርቅ የመፍታት ያለመ የሰላም ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።በዚህም ከኹለቱም ወገን በተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ችግሩን በእርቅ የመፍታት ሥነ ስርዓት የተካሄደ ሲሆን፤ የኮንፈረንሱ ተሳታፊ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የጸረ ሰላም ሀይሎችን ሴራ በማክሸፍ የቆየ አብሮነታችንን እናስቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።
የኹለቱ ህዝቦች የቆየ መልካም ግንኙነት ያላስደሰታቸው አካላት የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የአካባቢውን ሰላም ሲያውኩ መቆየታቸውንም በመጠቆም፤ የተፈጠረውን ያለፈ በደል ወደ ጎን በመተው በቀጠናው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አለማየሁ ባውዲ በሰላም ኮንፈረንሱ ላይ እንደገለጹት፤ የሰላም ትርጉሙ ሰፊ ቢሆንም ወንድማማችነት፣ ፍቅር፣ አብሮነት፣ መከባበር፣ እንዲሁም ነባር እሴትን በዘላቂነት አጎልብቶ አብሮ መኖርን ይጠይቃል ሲሉ አብራርተዋል።
በክልሉ በጋራ አብሮነት ላይ ተመስርተው በሚኖሩ የኮሬ እና የጉጂ ህዝቦች መካከል ሽብር በመፍጠር ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ አካል ጎድሏል፣ የግብይት እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ተቋማት መውደማቸውን በአብነትም ጠቅሰዋል።
ኹለቱ ህዝቦች ከዚህ በፊት የተፈጠረውን በደል ወደ ጎን በመተው እና የሰላምን አስፈላጊነት በመገንዘብ የቆየ አብሮነትን ለማስረጽ ባደረጉት ጥረት አሁን የተገኘው ሰላም ተፈጥሯል ብለዋል።
ህዝባዊ አብሮነትን ማስተሳሰር ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ያሉት አለማየሁ ታሪካዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ማስቀጠል የተዘጉ የመሰረተልማት ተቋማትን ማስቀጠል ይጠበቃል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኃይሌ ጉርሜሳ በበኩላቸው፤ ጸረ ሰላም ሀይሎች በፈጠሩት የሰላም እጦት ባለፉት ዓመታት በኹለቱ ተጎራባች ህዝቦች ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ መድረሱን አስታውሰዋል።
የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት እና ሰላምን ለማስፈን በተደረገ ጥረት የተዘጉ መንገዶች ተከፍተዋል፣ የጋራ የግብይት ሥፍራዎች እና መሰል ተቋማት ሥራ እንዲጀምሩ እንቅስቃሴ መደረጉንም ጠቁመዋል።
የአማሮ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ወገኔ ብዙነህ እንደገለጹት፤ የጉጂ ኦሮሞ እና የኮሬ ህዝቦች ለዘመናት የገነቡትን አብሮነት ተቻችሎ የመኖር እሴትን ለማፍረስ ያለመው ኦነግ ሸኔ ኹለቱን ህዝቦች ደም ሲያቃባ መኖሩን ተናግረዋል።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ፤ ኹለቱም ወንድማማች ህዝቦች ተለያይተው እንዲቆዩ ሚና የነበራቸው ጸረ ሰላም ኃይሎች እና የሽብር ቡድኖች ህይወት እንዲጠፋ እና ንብረት እንዲወድም ከማድረግ ባለፈ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና ዝርፊያ እንዲፈጸም ምክንያት መሆኑን መጠቆማቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ መረጃ ።
በዚህ በኹለቱ ተጎራባች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም ማስፈንን መሰረት ባደረገው የእርቅ ፕሮግራም ላይ የኹለቱም ክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣የሀይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ተነስተዋል የተባሉ ታጣቂ ቡድኖች አዋሳኝ በሆነችዉ በአማሮ ልዩ ወረዳ በሚገኙ አጎራባች ቀበሌዎች ላይ ከሐምሌ 2009 ጀምሮ በተደጋጋሚ በከፈቱት ጥቃት ለበርካታ ዜጎች ሞት፣ ለአካል ጉዳት እና ለንብረት ዉድመት እንዲሁም ከመኖሪያ ቤት መፈናቀል ምክንያት መሆኑ ይታወቃል።

The post በአማሮ ልዩ ወረዳ እና በምዕራብ ጉጂ ዞን አዋሳኝ ቀበሌዎች በሚኖሩ ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ያለመ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሄደ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply