በአምስት ዞኖች ላይ አሁንም የኮሌራ ወረርሺኝ መኖሩን የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡

ከተቀሰቀሰ 22 ወራትን ያስቆጠረዉ የኮሌራ ወረርሺኝ በአምስት ዞኖች ላይ አሁንም መኖሩን የክልሉ ጤና ቢሮ ለጣቢያችን አስታዉቋል፡፡

በባሌ አከባቢ ተነስቶ በ12 ዞኖች ከ87 በላይ ወረዳዎች ላይ የተከሰተዉን የኮሌራ ወረርሺኝ መቆጣጠር ቢቻልም አሁንም በአምስት ወረዳዎች ላይ እንደሚገኝ በክልሉ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ቁጥጥር እና አደጋ ምላሽ ሰጪ እንዲሁም የላቦራቶሪ አገልግሎት አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ከበበዉ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ነግረዉናል፡፡

አብዛኞቹን መቆጣጠር ቢቻልም የተወሰኑ ዞኖች እና ከተማ መስተዳደር ላይ ግን አሁንም ታካሚዎች እና ምልክቶች አሉ የሚሉት አስተባባሪዉ፤ሙሉለሙሉ ለመቆጣጠር የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸዉን ገልጸዋል፡፡

ወረርሺኙ ካለባቸዉ አምስት ዞኖች በሶስቱ ዞኖች ላይ ታካሚዎች መኖራቸዉን ያነሱት ዶ/ር ተስፋዬ፤ በቀሪዎቹ ሁለት ዞኖች ላይ ደግሞ ወደ 30 ቀናት አከባቢ ያልተመዘገበባቸዉ ቢሆንም እርግጠኛ ለመሆን የግድ 42 ቀናትን መጠበቅ እንደሚገባ ነዉ የገለጹት፡፡

አሁንም የኮሌራ ወረርሺኝ በምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ እንዲሁም በአርሲ ዉስጥ በሚገኙ 18 ወረዳዎች ላይ መኖሩን ነግረዉናል፡፡

በአምስቱ ዞኖች በተለይ ደግሞ በሶስቱ ዞኖች ላይ ኮሌራን በ8 ሳምንት ለማቆም በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረ ስራ መኖሩን አንስተዉ፤ የአየር ሁኔታዉ የሚመች ከሆነ እና ሌሎች ችግሮች ካልገጠሙ ኮሌራን በ2 ወራት ዉስጥ ለማጥፋት ስራዎች መጀመራቸዉን አንስተዋል፡፡

ከዚህ በፊት በክልሉ 11ሺህ6መቶ ሰዎች በኮሌራ ወረርሺኝ ተጠቅተዉ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

እስከዳር ግርማ
ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply