
በአስተዳደራዊ ድክመትና በንግግር ለከት ማጣት ሀገር የከፋ ቀውስ ውስጥ እየገባች ነው! መጋቢት 06 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት፣ መኢአድ እና ኢሕአፓ ፓርቲዎች የተሰጠ መግለጫ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ አልፎም በመረጡት ቦታ የመኖር መብት በሕገ መንግሥቱ ለዜጎች የተሰጣቸው መብት እንጂ አንዳንድ ባለስልጣናት ደስ ሲላቸው የሚቸሩት ካልፈለጉ ደግሞ የሚነፍጉት ጉዳይ አይደለም። ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚጓዙ መንገደኞች ላይ እናቶቻችን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት ሰበባ ሰበብ እየተፈለገ ሲፈጸም የነበረው ማዋከብ፣ እንግልትና ማጉላላት ከነገ ዛሬ መሻሻል ይታይበታል ተብሎ ተስፋ ሲደረግ ይባስ ብሎ “ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት መንግሥትን በመጣል በኃይል ስልጣን ለመቆጣጠር ያለመ ነው” በሚል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በቀን 5/07/2015 ዓ.ም ለምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ የገለጹበት መንገድ ያለፈውን ስህተት ከማረም ይልቅ የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት የሚነፍግ፣ በከፍተኛ ሴራና ፍረጃ ለበለጠው የዘር ፍጅት የሚያመቻችና ዜጎችን የማሸማቀቅ አካል ነው። በሌላ በኩል ትናንት ካህን በጥፊ ሲመቱ፣ ሕጻናትንና ሴቶችን ሲያዋክቡና በማንነታቸው ሲያሸማቅቁ፣ ሲሰውሩ፣ ሲገድሉና ሲዘርፉ ለኖሩ ኃይሎች ሽፋን የመስጠትና ጥብቅና የመቆም አካል አድርገን እንወስደዋለን። የክሩን ጫፍ ከተከተልነው ደግሞ እኩይ ድርጊቱ በኦሮሚያ ብልጽግና በንግግርም በተግባርም በተጠናና መዋቅራዊ በሆነ ኹኔታ እንደሚፈጸም ዐቢይ ማረጋገጫና በቀጣይም ሰቆቃና ማወከቡ ቢብስ እንጂ እንደማይረግብ ጉልህ ማሳያ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የሚከለከሉ ዜጎቻችን ጉዳይ የሌላ ሀገር ድንበር አቋርጠው በሕገወጥ መንገድ ለመግባት የሚሞክሩ መንገደኞች እንጂ ከሀገራቸው አንድ ክፍል አባቶቻቸው ወደአቀኑላቸው ዋና ከተማቸው የሚደረግ ሕጋዊ እንቅስቃሴ አይመስልም። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዓለም በድፕሎማቲክ ከተማነት በመጀመሪያዎቹ ረድፍ የምትጠቀስ፣ በሰላሟ የሚቀናባትን ከተማ በምዝበራና ወረራ እንድትጠቀስ፣ ነዋሪዎቿን በኑሮ ውድነት የምትጠብስ፣ ሌብነት ሕጋዊ ሆኖ እግር አውጥቶ የሚሄድባት፣ የአፍሪካና የመላ ጥቁር ሕዝብ ድልና ኩራት የሆነው አድዋ በባለቤቱ ሕዝብ የማይከበርባት፣ ጤፍ ብርቁ፣ ሲሚንቶ ብርቁ፣ ስኳር ብርቁ፣ የምሥኪን ዜጎቿን ጎጆ በግብታዊነትና በዘር ስካር የምታፈርስ ወደ ማድረግ አዘቅት መምራቱ ሳያንስ የንግግር ለከት ማጣቱና በጽንፈኛ ኃይሎች የተጻፈን ስክሪፕት(Script) በመንግሥት መዋቅር፣ በተከበረ ምክር ቤት ፊት አምጥቶ ማነብነብ እጅጉን ያስቆጣል። ምን አልባት ከዚህ ጀርባ ተስፋ መቁረጥ፣ በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ሀገር የመገንባት ቅዠት፣ ከተማዋን ጥቅም አልባ የማድረግ ቀጣይ ፕሮጀክት፣ ለጥፋቱና ለአጥፊዎች ሽፋን የመስጠት አካሄድ ይመስለናል። በሌላው ዓለም ቢሆን እንዲህ ያሉ እጅግ መርዘኛና ፍጅት ቀስቃሽ ንግግሮችና ተናጋሪዎች ተገቢው እርምት በቶሎ በተሰጣቸው ነበር። በእኛ ሀገር ኹኔታ ሕጋዊነት ሳይሆን ሕገ ወጥነት፣ “የእኛ” ሳይሆን “ለእኔ ብቻ” ባዮች፣ ተጠያቂነት ሳይሆን ተረኝነት የሰፈነበት በመሆኑ ለዚህ አልታደለንምና የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ሕግና ሥርዓት ሰፍኖ አጥፊዎች በፍትሕ አደባባይ እንዲቀርቡ የበኩሉን እንዲወጣ፣ እንዲህ ላሉ ከፋፋይ ንግግሮችም ጆሮ ባለመስጠት አንድነቱን እንዲያጸና ጥሪያችንን እናቀርባለን። ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ ኢሕአፓ፣ እናት ፓርቲ፣ መኢአድ መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24
Source: Link to the Post