በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩ እንዲፈቱ ኢሰመኮ አሳሰበ

  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩ እንዲፈቱ ኢሰመኮ አሳሰበ

   • በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የኢዜማ ሊቀመንበር ፍ/ቤት አልቀረቡም ተባለ
                 • አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ ባለፈው ረቡዕ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ

        በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ በአዋጁ ድንጋጌ መሰረት በእስር ላይ የሚገኙ ግለሰቦች እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አሳስቧል፡፡ ኮሚሽኑ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦችም  እንዲነሱ ጠይቋል፡፡
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ፣ በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ታስረው የነበሩ 19 እስረኞች፣ “የተሃድሶ ስልጠና” ከወሰዱ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ ከእስር መለቀቃቸው ተዘግቧል፡
ኢሰመኮ ላለፉት 10 ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሰብአዊ መብት ላይ የሚያደርሰውን ተፅእኖ በመከታተል፣ በአፈፃፀሙ ላይ ያሉ ጥሰቶችንና ክፍተቶችን ሲመረምር የቆየ ሲሆን፤ ግኝቶቹም በተከታታይ ሪፖርቶች  ታትመዋል፡፡
ኮሚሽኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸምን በተመለከተ ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም  ይፋ ባደረገው ሪፖርት፤ በክልሉ በግጭት ዐውድ ውስጥና ውጭ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሳሳቢ መሆናቸውን አስታወቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ በአዋጁ የተያዙ እስረኞችን መፍታት፣ ወደ መደበኛ የህግ ማስከበር አሰራር መመለስ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተጣሉ  የእንቅስቃሴ ገደቦችን ማንሳትና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት መመለስ እንደሚያስፈልግ ኮሚሽኑ በአፅንዖት አሳስቧል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታሰሩት ግለሰቦች  መካከል  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለውና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል አቶ ካሳ ተሻገርን የመሳሰሉ ታዋቂ ፖለቲከኞች  ይገኙበታል።
በፌደራል መንግሥትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተባባሰ የመጣውን ግጭት ተከትሎ፣ ባለፈው ዓመት ሃምሌ መጨረሻ ላይ  በአማራ ክልል ለ6 ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ የሚታወስ ሲሆን፤ ፓርላማው የመጀመርያው የስድስት ወራት ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ፣የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለተጨማሪ አራት ወራት ማራዘሙ ይታወቃል፡፡  
በሌላ በኩል፤ ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞ የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡ “ጦርነት ይቁም! ሰላም ይስፈን!” በሚል መሪ ቃል፣ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት የሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ ከሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ በተጨማሪ አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ ባለፈው ረቡዕ  ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
አቶ የሺዋስ አሰፋ “ሁከት በማነሳሳት” መጠርጠራቸውን አንድ የቤተሰብ አባል መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ፣ ህዳር 30 የተጠራው ሰልፍ አስተባባሪ ነበሩ የተባሉት አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ ባለፈው ረቡዕ  መሳለሚያ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተይዘው መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  

Source: Link to the Post

Leave a Reply