በአንድ ዓመት በኢትዮጵያ በ594 አጋጣሚዎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መከሰቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በአጠቃላይ በ202 እስር ቤቶችን ጨምሮ ወደ 600 ያህል ምርመራዎችን በባለሙያዎች ሲያካሂድ መቆየቱን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን አሳሳቢ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች የሚፈጸምባት አገር እንደሆነች አረጋግጫለሁ ይላል፡፡

በተጨማሪ አኃዞች ለማስደገፍ የሞከረው የኮሚሽኑ ሪፖርት በ2023 በኢትዮጵያ የተመዘገበው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አኃዝ ከቀደመው 2022 ዓመት በ55.9 በመቶ የጨመረ መሆኑን ይገልጻል፡፡

በዓመቱ ወደ 18 ጊዜ የድሮን ጥቃቶችን በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ መንግሥት መፈጸሙን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡

በእነዚህ የድሮን ጥቃቶችም 248 ንፁኃን ተገድለው 55 መቁሰላቸውን ይጠቅሳል፡፡

መንግሥት ድሮንን ለውጊያ ማዋሉ ፍጹም የማይመጣጠን የጦር መሣሪያ ከማዋል ባለፈ፣ ለብዙ ሲቪሎች ሞትና መጎዳት ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ይናገራል፡፡

ሪፖርቱ በክልል ደረጃ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን በአኃዞች ለማነፃፀር ይሞክራል፡፡

በአማራ ክልል እጅግ አሳሳቢ የሆኑ ጥፋቶች መመዝገባቸውን በመጠቆም፣ በክልሉ በአጠቃላይ 179 አጋጣሚዎች መከሰታቸውንና 3,163 ሰዎች ሰለባ መሆናቸውንም ያስረዳል፡፡

እንደ መርአዊ ባሉ ከተሞች የደረሰውን የ89 ሰዎች ግድያ ጨምሮ በባህር ዳርና በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ማጋጠሙን ይናገራል፡፡

በክልሉ በድምሩ 740 ሰዎች መገደላቸውንም ይጠቁማል፡፡
በተለይ የአማራ ክልል ጦርነት ከተጀመረ በኋላ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሥራ ላይ በዋለባቸው ወራቶች የአማራ ተወላጆችን ዒላማ ያደረገ እስርና ሌላም የሕግ ጥሰቶች መፈጸማቸውን ሪፖርቱ ይዘረዝራል፡፡

በክልሉ ወደ 39 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ወደ ጦር ካምፕነት ተለውጠው የታዳጊዎች የመማር መብት ተነፍጎ እንደነበርም ያትታል፡፡

ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ ባሉት የአውሮፓውያኑ 2023 ዓመት ወራቶች 107 ጊዜ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎች ማጋጠማቸውን በመጥቀስ፣ በዚህም 71 ሴቶችን ጨምሮ በድምሩ 2,424 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ይጠቁማል፡፡

በአማራ ክልል የፋኖ ኃይሎችም ቢሆን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት መሆናቸውን የሚናገረው ሪፖርቱ፣ ይሁን እንጂ መከላከያን ጨምሮ የአማራ ክልል ፖሊሶችና ሚሊሻዎች ዋነኞቹ የጥሰት ምንጮች ናቸው ይላል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ደግሞ በ188 አጋጣሚዎች 1,488 ሰዎችን ለጉዳት የዳረጉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጠራቸውን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

በነዚህ አጋጣሚዎች ደግሞ በድምሩ የ366 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ ይሁን እንጂ በኦሮሚያ ከመንግሥት አካላት ይልቅ መንግሥታዊ ባልሆኑ ኃይሎች የሚደርሰው ጉዳት እንደሚብስ ይጠቁማል፡፡

ከኦነግ ሸኔ ኃይሎች ጋር የሚካሄደው ጦርነት ዋናው የሰብዓዊ መብቶችን መጣስ እያስከተለ ያለ ጉዳይ ቢሆንም፣ በኦሮሚያ በታጠቁ ኃይሎች የሚካሄደው ጥቃትም ከባድ ሥጋት መሆኑን ይጠቁማል፡፡

ሪፖርቱ በዚህ ዓመታዊ ግምገማው በኢትዮጵያ ከሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ አብላጫዎቹ ወይም 70 ከመቶዎቹ በመንግሥት ኃይሎች የተፈጸሙ ናቸው ይላል፡፡

የኤርትራ ኃይሎችን ጨምሮ መንግሥታዊ ያልሆኑ ሌሎች ኃይሎችም የመብት ጥሰቶች ምንጭ ናቸው ይላል፡፡

ሰኔ 11ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply