You are currently viewing በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ታስረው ከነበሩ እስረኞች መካከል አስራ ዘጠኙ መፈታታቸው ተነገረ

በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ታስረው ከነበሩ እስረኞች መካከል አስራ ዘጠኙ መፈታታቸው ተነገረ

በሙሉጌታ በላይ

በአፋር ክልል በሚገኘው አዋሽ አርባ የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ በእስር ላይ ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ጋዜጠኞች መካከል አስራ ዘጠኙ “የተሃድሶ ስልጠና’’ ከወሰዱ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ መለቀቃቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በተመሳሳይ ቀን ሌሎች 20 እስረኞች ከአዋሽ አርባ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የእስረኞች ማቆያ እንዲዘዋወሩ መደረጋቸውን እና ነገ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።

እስረኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ በዋነኛነት በአማራ ክልል እና እንዳስፈላጊነቱ ደግሞ “በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ” ተፈጻሚነት እንዲኖረው ከተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ነው። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ ባወጣው መግለጫ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ እና ከአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ተይዘው በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ወደሚገኝ “መደበኛ ያልሆነ ማቆያ ጣቢያ” የተወሰዱ እስረኞች ብዛት 53 መሆናቸውን አስታውቆ ነበር። 

ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፤ የጸጥታ አካላት “የማጣራት ሥራዎችን በመስራት” አዋሽ አርባን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች “ያለአግባብ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች እንዲለቀቁ” ማድረጋቸው” እና “የተወሰኑትም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጉን” ጠቅሶ ነበር። ኢሰመኮ በሪፖርቱ ከጠቀሳቸው ከእስር የተለቀቁ ፖለቲከኞች መካከል፤ የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ አመራሮች የሆኑት አቶ ጊደና መድኅን እና አቶ ካልአዩ መሀሪ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ኃይማኖት ይገኙበታል። 

ኮሚሽኑ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርቱ፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የቀድሞ አባል የሆኑት መምህር ናትናኤል መኮንን፣ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ እና ጋዜጠኛ አብነት ታምራት በአዋሽ አርባ በእስር ላይ እንዳሉ አስታውቆ ነበር። ሆኖም መግለጫው ከወጣ በኋላ መምህር ናትናኤል እና ጋዜጠኛ አብነት ከእስር መለቀቃቸውን ማረጋገጡን በኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ስራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በኢሰመኮ የነሐሴ ወር ሪፖርት ተጠቅሰው የነበሩት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ እና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ስንታየሁ ቸኮል፤ ግንቦት 25፤ 2016 ከአዋሽ አርባ ወደ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደተዘዋወሩ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል። “የኢትዮ ኒውስ” የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን መስራች የሆነው ጋዜጠኛ በላይም በቢሮው ስር ወዳለው የእስረኞች ማቆያ መዘዋወሩንም አክለዋል። 

ባለፈው ህዳር ወር መጀመሪያ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋለው ጋዜጠኛ በላይ፤ በአዋሽ አርባ ታስረው ከቆዩ ሌሎች እስረኞች ጋር ባለፈው ሳምንት ሰኞ ግንቦት 19፤ 2016 ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ መደረጉን ባለቤቱ በላይነሽ ንጋቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር’’ ተናግረዋል። ጋዜጠኛው እንደ ሌሎቹ እስረኞች ሁሉ “ለተሃድሶ ስልጠና’’ ከተወሰደ ከአንድ ቀን በኋላ፤ አሁን ወደሚገኝበት የአዲስ አበባ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንዲመለስ መደረጉን ባለቤቱ አመልክተዋል።

ጋዜጠኛ በላይ ከሌሎቹ እስረኞች ተለይቶ በስልጠናው እንዳይካፈል እና እንዳይፈታ የተደረገበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንዳልተነገረውም ባለቤቱ ጨምረው ገልጸዋል። ለቀሪዎቹ 19 እስረኞች፤ ለአምስት ቀናት የቆየ “የተሃድሶ ስልጠና’’ የተሰጠው በአዲስ አበባ ኮልፌ አካባቢ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ “ፈጥኖ ደራሽ ማሰልጠኛ ማዕከል” መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ አንድ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል።

እስረኞቹ በኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ማሰልጠኛ ቆይታቸው፤ “የሰላም ሰነድ” የሚል ስያሜ ያለው ባለ 20 ገጽ ሰነድን መነሻ በማድረግ ስልጠና እንደተሰጣቸው እኚሁ ምንጭ ጠቁመዋል። ከአዋሽ አርባ ወደ አዲስ አበባ ስለተዘዋወሩ እስረኞች እና ተሰጥቷቸዋል ስለተባለው ስልጠና ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የፌደራል ፖሊስ ቃል አቃባይ ጄይላን አብዲ፤ ጉዳዩ በምርመራ ላይ ስለሆነ ማብራሪያ መስጠት እንደማይችሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ባለፈው ቅዳሜ ከእስር የተለቀቁትን ጨምሮ በአጠቃላይ 40 እስረኞች ከአዋሽ አርባ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መደረጋቸው ቢገለጽም፤ በወታደራዊ ካምፑ ውስጥ በሚገኘው የእስረኛ ማቆያ የቀሩ እስረኞች እንዳሉ ምንጮች ተናግረዋል። ከእነዚህ እስረኞች መካከል “አልፋ ሚዲያ” የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን መስራች እና አዘጋጅ ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው እንደሚገኝም ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Source: Link to the Post

Leave a Reply