
በአዲስ አበባ ቤት የፈረሰባቸውን ሰዎች ቅሬታ ለመቀበል የሄዱ የዓባይ ቴሌቪዥን የቀረጻ ባለሙያዎች ታሰሩ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 9 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ማክሰኞ ጥር 9 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቤት የፈረሰባቸውን አቤቱታ አቅራቢዎች ለማነጋገር የሄዱ የዓባይ ቴሌቪዥን የቀረጻ ባለሙያዎች ከእነ አቤቱታ አቅራቢዎቹ መታሰራቸው ተገልጧል። ጥር 9/2015 ከረፋዱ አምስት ሰዓት አካባቢ፤ በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ቤት ፈረሰብን ያሉ አቤቱታ አቅራቢዎችን ሁኔታ በአካል ለመመልከትና ዘገባ ለመስራት በሥፍራው የደረሱት የዓባይ ቴሌቪዥን ”ካሜራ ማን“ እና ባልደረባው ቀረጻውን ተከልክለው በጸጥታ ሃይሎች መወሰዳቸውን የቀረጻ ባለሙያው እስሩ በተፈጸመበት ወቅት ወደ ቢሮ በመደወል አሳውቆናል ሲል የቴሌቪዥን ጣቢያው ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡ ነገር ግን ባለሙያው መታሰራቸውንና ወደ ጣቢያ እየወሰዷቸው እንደሆነ ካሳወቀ በኋላ የጸጥታ ሃይሎች ስልኩን ስለተቀበሉት ወዲያውኑ እንደተዘጋና እንደማይሰራ የጣቢያው ባልደረቦች ጨምረው አስረድተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በተደረገ ማጣራት የታሰሩት የሚዲያው ባልደረቦች የካ አባዶ አካባቢ ወረዳ አስራ ሦስት ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ ማወቅ መቻሉን የሚዲያው ሃላፊዎች ተናግረዋል ሲል የዘገበው አዲስ ማለዳ ነው።
Source: Link to the Post