በአዲስ አበባ ትላንት ማምሻዉን በደረሱ ሦስት የእሳት አደጋዎች በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የእሳት አደጋና ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
በዚህም ትላንት ማምሻዉን 11:26 በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አደይ አበባ አካባቢ በአጋጠመ የእሳት አደጋ በኹለት ሆቴሎችና በአንድ ፔንሲዮን ላይ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል።
ኹለተኛዉ አደጋ ያጋጠመዉ ምሽት 12:20 ሰዓት ንፋሰ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ሲሆን፤ በአንድ ባጃጅ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ባጃጇ ሙሉ በሙሉ መቃጠሏ ተገልጿል።
በተጨማሪም ሦስተኛዉ አደጋ ያጋጠመዉ ምሽት 3:05 ሰዓት ላይ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ዘነበ ወርቅ ባጃጅ ተራ ሲሆን፤ በአጋጠመው የእሳት አደጋ የተለያዩ የንግድ አገልግሎት የሚሰጥባቸዉ 6 የንግድ ቤቶች ተቃጥለዋል።
ሦስቱንም የእሳት አደጋዎች ለመቆጣጠር አምስት ሰዓት የፈጀ ሲሆን፤ በደረሱት የእሳት አደጋዎች በሰዉ ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩም ተገልጿል።
Source: Link to the Post