በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ አካባቢ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሁለት የፋኖ አመራሮችን መግደሉን ፖሊስ አስታወቀ

በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ፣ ፖሊስ የፋኖ አባላት ናቸው ካላቸው ግለሰቦች ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርጎ ሁለቱን መግደሉንና አንዱን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሰጠው መረጃ መሠረት፤ ዛሬ አርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ፖሊስ ክትትል ሲያደርግባቸው በነበሩ የቡድኑ አባላት ላይ እርምጃ ወስዶ አመራር ነው የተባለ ግለሰብ ተገድሏል ብሏል።  ፖሊስ  “የፋኖ አመራሮች” ናቸው ካላቸው  ታጣቂዎች ጋር ባደረገው  የተኩስ ልውውጥ፤ ሁለቱ ሲገደሉ አንዱ ጉዳት ሳይደርስበት መያዙን ገልጿል። በተኩስ ልውውጡ ወቅት ሁለት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትን ጨምሮ አራት ሰዎች መቁሰላቸውን ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ፖሊስ  የፋኖ አባላት ናቸው ባላቸው ናሁሰናይ አንድአርጌ ታረቀኝ፣ አቤኔዜር ጋሻው አባተ እና ሀብታሙ አንድአርጌ ተሰማ ላይ  ክትትል ሲያደርግ  መቆየቱን ገልጾ፤ ዛሬ  ሚያዚያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር ለማዋል ሲሞክር  ተጠርጣሪዎቹ ዲዛዬር መኪና በመጠቀም በፖሊስ አባላት ላይ ተኩስ በመክፈት ሊያመልጡ መሞከራቸውንም ገልጿል። በዚህ የተኩስ ልውውጥ ፖሊስ የፋኖ መሪ ነው ያለው ናሁሰናይ አንዳርጌ ታረቀኝ ከቆሰለ በኋላ ወደ ህክምና ተወስዶ ሕይወቱ አልፏል ብሏል።

ፖሊስ፤ “ናሁሰናይ አንዳርጌ የሚባለው ተጠርጣሪን  በፖሊስ ቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረገው እንቅስቃሴ እጅ ላለመስጠት ከፍተኛ የሆነ ትግል ማድረጉን ገልጾ፤ በዚያ አካባቢ የሚሄድ አንድ ግለሰብ ሕይወት ማለፉንና  ሳጅን አራርሳ ተሾመና ኮንስታብል ማቲያስ ጴጥሮስ የተባሉ የፖሊስ አባላት ላይ  ከባድ ጉዳት መድረሱን ጠቁሟል።

ሀብታሙ አንዳርጌ ተሰማ በተኩስ ልውውጡ መሃል መገደሉን የገለፀው ፖሊስ፤ አቤኔዘር ጋሻው አባተ የተባለው ሦስተኛው ተጠርጣሪ ምንም ጉዳት ሳይደርስበት በቁጥጥር ስር መዋሉን  አስታውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply