
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቅዱስ ሲኖዶስን ትዕዛዝ ተከትሎ ጥቁር የለበሱ የመንግስት ሰራተኞችን ከስራ እና ከደመወዝ ማገዱ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑ ተገለጸ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቅዱስ ሲኖዶስን ትዕዛዝ ተከትሎ ጥቁር የለበሱ የመንግስት ሰራተኞችን ወደ ቢሮ አትገቡም በሚል በግልጽ በደብዳቤ ከከለከሉት ተቋማት በላይ በቴሌግራም እና በቢሮ ውስጣዊ አሰራር በሰራተኞች ላይ ክልከላ እና ጫና ያደረጉ ብዙ ናቸው። እንደአብነትም ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን እና ሌሎች አንዳንድ ተቋማትም ሰራተኞች ጥቁር ልብስ ለብሰው አገልግሎት እንዳይሰጡ መከልከላቸው ይታወሳል። አሁን ላይ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንዳመለከቱት ጥቁር ለብሰው ጾመ ነነዌን ባሳለፉ የመንግስት ሰራተኞች ላይ ጫና እየደረሰባቸው ነው። የዚህ ውሳኔ ተጠቂ ከሆኑት መካከል አንዷ በለጡ ዘለቀ መርሻ ይባላሉ። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ በህግ እና ቴክኒክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የድጋፍ እና ክትትል ቅሬታ አቤቱታ አፈታት ስራ አመራር ባለሙያ የስራ ስምሪት ባለሙያ ናቸው። ቢሮው በለጡ አጠፉት የተባለውን ጥፋት በደፈናው በማለፍ “ከተሰጥዎት ተግባር እና ኃላፊነት ውጪ ተሳትፈው የተገኙ በመሆንዎ” በማለት፣ ጉዳዩም በተቋሙ የዲስኘሊን ኮሚቴ ታይቶ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ከስራ እና ደመወዝ አግዶ ማቆየት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል በሚል የስራ እና የደመወዝ እገዳ ማድረጉን አመላክቷል፡፡ በዚህ መሰረት ከየካቲት 1/2015 ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 56/2010 አንቀጽ 72 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ከስራና ደመወዝ የታገዱ መሆኑን አሳውቃለሁ ሲሉ ኃላፊው ደብዳቤ እንዲደርሳቸው አድርገዋል፡፡ እግድ የተፈጸመባቸው በለጡም “የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ጥቁር ልብስ ለብሳችሁ ቢሮ አትገቡም ለምን ተባልን በሚል ድምፄን በማሰማቴ ከስራና ደመወዝ የሚያግድ ደብዳቤው በተፃፈ በ13 ቀኑ ዛሬ ማገጃው ደርሶኛል፤ እንኳን መታገድ መሞት አለ።” የሚል አስተያየታቸውን በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አጋርተዋል።
Source: Link to the Post