በአዲስ አበባ የልደት ሰርተፊኬት በጤና ተቋማት መስጠት መጀመሩ ተገለጸ

ረቡዕ ኀዳር 14 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት የልደት ሰርተፍኬት በነፃ መሰጠት መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዮናስ አለማየሁ በከተማዋ በሚገኙ የጤና ተቋማት ከዚህ በፊት የልደት ሰርተፍኬት እንደማይሰጥ አስታውሰው፤ ይህም በአገሪቷ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሙሉ ለሙሉ ለማወቅ አዳጋች ማድረጉን ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ መንግስት በየአመቱ የሚበጅተው በጀት ከተማሪ ምገባ፣ ዩኒፎርምና ለትምህርት ቤቶች የሚያስፈልገው የመምህር ብዛት እንዳይታወቅ አድርጎታል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ምን ያህል ህፃናት እንደተወለዱ፣ ምን ያህል ዜጎች እንደተጋቡና እንደሞቱ መታወቅ አለበት ብለዋል።

በመሆኑም በከተማዋ በሚገኙ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት የልደት ሰርተፍኬት በነፃ በመሰጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህም ቴክኖሎጂን ቀዳሚ አድርገን እየተንቀሳቀስን ነው ሲሉ መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በጤና ተቋማቱ ባለሙያ ተመድቦ ምዝገባ እየተከናወነ ይገኛል። የልደት ሰርተፊኬቱ በ33 የጤና ተቋማት እየተሰጠ ሲሆን፤ እናቶች ልጆቻቸውን አስመዝግበው በተወለዱበት ቀን ሰርተፍኬት እየተቀበሉ ይገኛሉ።

አገልግሎቱ በግል የጤና ተቋማት እየተሰጠ ሲሆን ከመንግስት የጤና ተቋማት ውስጥ ዘውዲቱ፣ ጋንዲ፣ ጴጥሮስና ጳውሎስን የመሳሰሉት እንደሚገኙበት የተገለጸ ሲሆን፤ እነዚህም አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ውልደት የሚከሰትባቸው የጤና ተቋማት ናቸው።

The post በአዲስ አበባ የልደት ሰርተፊኬት በጤና ተቋማት መስጠት መጀመሩ ተገለጸ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply