አዲስ ከተማ ፣ ኮልፌ እንዲሁም አቃቂ ክፍለ ከተሞች በአዲስ አበባ ከሚገኙ 11 ክፍለ ከተሞች መካከል ለጎርፍ አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ የተጋለጡ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
የእሳት እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግኑኝነት ሀላፊ አቶ ጉልላት ጌታነህ ለጣቢያችን እንደተናገሩት ፣በአዲስ አበባ ከተማ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተማ የጎርፍ ተጋላጭነት መጠን መጠናቱን ተናግረው፣ ወደ 363 ቦታዎች ተለይተዋል ብሏል፡፡
እነዚህ ተጋላጭ ቦታዎች በብዛት በአዲስ ከተማ ፣ በኮልፌ እንዲሁም አቃቂ ክፍለ ከተሞች አንደሚገኙ በጥናቱ መለየቱን አስታውቀዋል፡፡
ከነዚህ ሶስት መቶ ስልሳ ሶስት ቦታዎች መካከል 226 ቦታዎች በከፍተኛ ሁኔታ በጎርፍ የመጋለጥ አጋጣሚ ያላቸው መሆኑ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡
እንደዚሁም 120 ቦታዎች መካከለኛ ጎርፍ የመጋለጥ አዝማምያ ያለ ሲሆን 17 ቦታዎች ደግሞ ዝቅተኛ በጎርፍ የመጋለጥ አጋጣሚ መኖሩ በጥናት መረጋገጡን ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው፡፡
ለጎርፍ አደጋ መከሰት እንደ ምክንያት የሚነሳው ከተማዋ የመሬት አቀማመጥ፣ ከተማዋ በፕላን ያልሰራች መሆኑ ፣በተለያዩ ቦታዎች ያሉት የፍሳሽ ማስወገጃዎች በቆሻሻ መሞላት እና በከተማዋ በልማት ሰበብ የሚቆፈሩ ጉድጓዶች ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተናብው አለመስራትም እንዲሁም ለካባ ድንጋይ ማውጫ ተብለው የሚቆፈሩ ቦታዎችን መልሶ አለመድፍን ለጎርፍ አደጋ መከሰት በምክንያትነት መጠቀሳቸውን በጥናቱ መመላከቱ ተጠቅሷል፡፡
ወቅቱ ከፍተኛ ዝናብ የሚጥልበት ጊዜ በመሆኑ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያሳሰቡት አቶ ጉልላት ጌታነህ ፣ክረምቱን ተከትሎ የሚከሰተው የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ኮሚሽኑ ቅድመ የመከላከል ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውቋል፡፡
ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም
Source: Link to the Post