You are currently viewing በአዲስ አበባ የተለያዩ ት/ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ባንዴራን እና መዝሙርን በኃይል ለማሰቀል እና ለማዘመር የተደረገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ የተፈጠረውን ግጭት ለማርገብ የጸጥታ አካላት የወሰዱት…

በአዲስ አበባ የተለያዩ ት/ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ባንዴራን እና መዝሙርን በኃይል ለማሰቀል እና ለማዘመር የተደረገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ የተፈጠረውን ግጭት ለማርገብ የጸጥታ አካላት የወሰዱት…

በአዲስ አበባ የተለያዩ ት/ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ባንዴራን እና መዝሙርን በኃይል ለማሰቀል እና ለማዘመር የተደረገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ የተፈጠረውን ግጭት ለማርገብ የጸጥታ አካላት የወሰዱት እርምጃ የህጻናትን መብት የሚጥስ ተግባር ስለመሆኑ ኢሰመኮ በሪፖርቱ አመለከተ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 20 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር ውዝግብና ተያያዥ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎችን በተመለከተ ኢሰመኮ ሪፖርት አውጥቷል። ኢሰመኮ በአዲስ አበባ የተለያዩ ት/ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ባንዴራን እና መዝሙርን በኃይል ለማሰቀል እና ለማዘመር የተደረገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት ብዙ ሕፃናት ተማሪዎችን የተሟላ አገልግሎት በሌላቸውና ለአካለ መጠን የደረሱ ተጠርጣሪዎች በሚታሰሩባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች አስረው ማቆየታቸው የአስፈላጊነት፣ የሕጋዊነትና የተመጣጣኝነት መርሆችን ያልተከተለ የሕፃናትን መብቶች የሚጥስ ተግባር ነው ሲል ወቅሷል፡፡ በትምህርት ቤቶቹ ግቢ ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማን ከፌዴራሉ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ጎን በመስቀልና ጠቅላላው ተማሪዎች የክልሉን መዝሙር በመዘመር የሰንደቅ ዓላማ ሥርዓቱን እንዲያከብሩ በመደረጉ በየትምህርት ቤቶቹ በሚገኙ ከፊል የትምህርት ቤቶቹ ማኅበረሰብ አባሎች እርምጃው ሕጋዊ መሠረት የለውም በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል ሲልም አክሏል፡፡ በአብዛኛው አካባቢዎች በተፈጠረ ሁከት፣ ረብሻና ግጭት፤ እንዲሁም የፖሊስ አባላት ሁኔታውን ለመቆጣጠር በወሰዱት የእስር እርምጃ የሰብአዊ መብቶች አሉታዊ አንድምታ ያስከተለ ሁኔታ ተፈጥሯልም ብሏል፡፡ የትምህርቱ ሂደት በመስተጓጎሉ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በተወሰኑ ተማሪዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ከባድና ቀላል የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሷል። የተማሪዎችና የትምህርት ቤቶች ንብረት ወድሟል፣ ሕፃናት ተማሪዎች ለአካላዊ እንግልት እና ከሕግ ውጭ ተገቢ ላልሆነ እስር ተዳርገዋል፡፡ ይሁንና በማኅበራዊ ሚዲያ እና በአንዳንድ ተቋሞችም የተዘገበውና ጉራራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ከፍተኛ 12 ትምህርት ቤት ውስጥ የነበረ ተማሪ ሕይወት ጠፍቷል የተባለው ትክክለኛ መረጃ አለመሆኑንና በዚህ ክስተት የደረሰ የሕይወት መጥፋት አለመኖሩን ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡ ምንም እንኳ አብዛኞቹ የተፈቱ መሆናቸውን የጠቀሰው ኢሰመኮ እጅግ ብዙ ዕድሜያቸው በአብዛኛው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ተማሪዎች ከመነሻውም ቢሆን ለእስር መዳረጋቸው እና ለተለያየ ጊዜ መጠን በእስር መቆየታቸው ተገቢ ያልሆነና ለነገሩ ሁኔታም ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ነው ብሎታል፡፡ የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ በሆነ እርምጃ ሁከቱን በመቆጣጠር፣ እጅግ ቢበዛ ሁኔታው እስኪረጋጋ ድረስ ተማሪዎቹን በየትምህርት ቤታቸው ግቢ ወይም ባሉበት ቦታ እንዲቆዩ አድርገው፣ በቀጥታ በወንጀል ተግባር ላይ የነበሩ ተማሪዎች ካሉም እንደአስፈላጊነቱ እጅግ አጭር ለሆነ ጊዜ ብቻ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቆይተው እንደአግባብነቱ በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 28(1) መሰረት በፖሊስ ጣቢያ በሚሰጥ ዋስትና መልቀቅ ይገባቸው እንደነበር ገልጧል። ከዚህ ውጪ ግን ብዙ ሕፃናት ተማሪዎችን የተሟላ አገልግሎት በሌላቸውና ለአካለ መጠን የደረሱ ተጠርጣሪዎች በሚታሰሩባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች አስረው ማቆየታቸው የአስፈላጊነት፣ የሕጋዊነትና የተመጣጣኝነት መርሆችን ያልተከተለ የሕፃናትን መብቶች የሚጥስ ተግባር ነው፡፡ በተማሪዎች ተፈጽሟል የሚባል ጥፋት ቢኖርም እንኳን ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በሚመለከተው የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችና አግባብነት በአላቸው የኢትዮጵያ ሕጎች መሠረት ለሕፃናት ልጆች የሚገባው የሕግ ከለላ እንደተጠበቀ ሆኖ የማጣራት ሥራ ከማከናወን በስተቀር፤ ሕፃናት ተማሪዎችን ሊያውም በጅምላ ለእስር መዳረግ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እርምጃ በመሆኑ ለወደፊቱ ሊደገም የማይገባ ነው ሲል አሳስቧል፡፡ ለዚህ ሁከትና ለደረሰው የሰብአዊ መብቶች ጉዳት መነሻ ምክንያት የሆነውን የሰንደቅ ዓላማ እና የብሔራዊ መዝሙር አጠቃቀም ሕጋዊነትን አለመከተል መሆኑን ጠቁሟል። የአንድ ክልል ሰንደቅ ዓላማ በሌላ ክልል ወይም ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ወይም የግል ተቋሞች ውስጥ እንዲሰቀል የሚያስችል የሕግ መሠረት የለም፡፡ ከሕጋዊና ምክንያታዊ የሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ውጪ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ውስጥ የሚገኙ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ወይም የሕዝብ አገልግሎት ተቋሞች የሌላ ክልል ሰንደቅ ዓላማን በአስገዳጅነት ለመስቀል መጣር ሕጋዊ መሠረት የሌለው ከመሆኑም በላይ አላስፈላጊ ውዝግብና ሁከት በመፍጠር ለሰብአዊ መብቶች መጣስ ሥጋት የሚፈጥር ድርጊት በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው ብሎታል፡፡ በተመሳሳይ ሕጋዊና ምክንያታዊ ከሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር አጠቃቀም ውጪ የአንድ ክልል መዝሙርን ለማዘመር መሞከርም አላስፈላጊ ውዝግብና ሁከት መፍጠር ለሰብአዊ መብቶች መጣስ ሥጋት የሚፈጥር ድርጊት በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ስለመሆኑ ጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት በሰብአዊ መብቶች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ውሳኔዎች፣ ደንቦች፣ ፕሮግራሞች፣ መርኃ ግብሮች ወይም አሠራሮች ሲያዘጋጁ ወይም ከመተግበራቸው በፊት በሰብአዊ መብቶች ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን አሉታዊ ውጤቶች አስቀድሞ መለየት፣ ማጤንና መከላከል ወይም መቀነስ የሚቻልበትን መንገድ ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል ነው ያለው ኢሰመኮ በሪፖርቱ። በትምህርት ቤቶች ውስጥ አመጽ፣ ማስፈራራትና የኃይል እርምጃ የሕፃናት ልጆችን በምቹ ሁኔታ የመማርና የማደግ መብት የሚጎዳ፣ ለሥነ ልቦና ጉዳት የሚያጋልጥ እና አጠቃላይ የሆነ ፍርሀት፣ ሥጋትና ጭንቀት በማሳደር ትምህርትን፣ ዕውቀትንና ዕድገትን የሚጎዳ በመሆኑ ይህን መሰል ሥጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን በሙሉ ማስወገድ አስፈላጊ ነው፣ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሕፃናት ልጆች የሰው ልጆች ክቡርነትና እኩልነትን፣ የሃሳብ ልዩነትና መቻቻልን እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ሙሉ እሴቶችን በሰላማዊ መንገድ የሚማሩበት የሚለማመዱበት እና የሚያጎለብቱበት ስፍራ ስለሆነ፤ ሕፃናት ልጆችን እና ተማሪዎችን በሚመለከታቸው ጉዳይ በማማከር፣ በማሳተፍና በማድመጥ የትምህርት ቤታቸው ሕይወት ውስጥ ፈቃደኛ ተሳታፊዎች ማድረግ እንጂ በኃይል፣ በዛቻ፣ በማስፈራራት፣ በማስጨነቅና በሥጋት ማስተማርና ማስተዳደር ተገቢ አይሆንም ሲል አውግዟል፡፡ ልጆች በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ፣ ሃሳባቸውን እና ተቃውሟቸውን የመግለጽ ነጻነት ያላቸው እንደመሆኑ መጠን አስፈላጊ ክህሎቶችን የሚያጎለብቱበትን መብታቸውን በአግባቡ የሚጠቀሙበትን ምቹ ሁኔታ እና ድጋፍ በትምህርት ቤቶች ውስጥም ማመቻቸት ተገቢ ነው ብሏል። በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን:- ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ወደፊትም እንዳያጋጥሙ ለችግሩ መንስኤ ለሆነው የሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር ውዝግብ ሕፃናትን ጨምሮ ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ግልጽ የሆነ የሕግ እና ፖሊሲ መፍትሔ በማበጀት ዘላቂ እልባት በመስጠት፣ እንዲሁም አሁን በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎች እና የሰብአዊ መብቶች መርሆችን በማክበርና በማስከበር የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በጋራ እንዲከላከሉ፤ በተጨማሪም የየትምህርት ቤቶቹና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ በሰላም፣ በመቻቻል እና የሃሳብ ልዩነትን በመቀበልና በሰላማዊ መንገድ ብቻ በመፍታት ላይ ተመሥርቶ የመፍትሔ አካል እንዲሆን አበክሮ አሳስቧል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply