በሃሚድ አወል
ለአምስት ዓመታት ያህል ጭማሪ ማሻሻያ ሳይደረግበት የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ የአውቶብስ ትራንስፖርት ታሪፍ ላይ 56 በመቶ ጭማሪ ተደረገ። በሚኒባስ ታክሲ የህዝብ ትራንስፖርት ታሪፍ ላይም፤ ከ50 ሳንቲም እስከ ሁለት ብር ድረስ ጭማሪ መደረጉ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ዛሬ አርብ ጥር 12፤ 2015 ይፋ ባደረገው ማሻሻያ መሰረት፤ አንድ ብር ከ50 ሳንቲም የነበረው ዝቅተኛ የከተማ አውቶብስ ታሪፍ ወደ ሶስት ብር ከፍ ብሏል። ሃያ ብር የነበረው ከፍተኛ የከተማ አውቶብስ ታሪፍ ደግሞ የአምስት ብር ጭማሪ ተደርጎበት 25 ብር ገብቷል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የከተማ አውቶብስ ታሪፍ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገው ታሪፉ ከተሻሻለ “ረጅም ጊዜ” ስላስቆጠረ እና “አስተዳደራዊ እና operational ወጪዎች በመጨመራቸው” ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል። በአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ታሪፍ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ማሻሻያ የተደረገው በህዳር 2011 ዓ.ም ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ቢሮው ማሻሻያ ያደረገበት ሌላኛው የትራንስፖርት አማራጭ፤ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ነው። በጭማሪው መሰረት አራት ብር የነበረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ታሪፍ ሰባት ብር ሆኗል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
The post በአዲስ አበባ የአውቶብስ ትራንስፖርት ታሪፍ ላይ የ56 በመቶ ጭማሪ ተደረገ appeared first on Ethiopia Insider.
Source: Link to the Post