
በአዲስ አበባ የአድዋ ቲሸርት እንዳያትሙ በፖሊስ መከልከላቸውን ማተሚያ ቤቶች ገለጹ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በአዲስ አበባ የሚገኙ ማተሚያ ቤቶች በሚቀጥለው ሐሙስ ለ127ኛ ጊዜ ለሚከበረው ለአድዋ ድል በዓል ቲሸርት እንዳያትሙ በፖሊስ መከልከላቸውን ገልጸዋል፡፡ ከኢትዮጵያን አልፎ የጥቁሮች ኩራትና የነጻነት ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰደው የአድዋ ድል በዓል በየዓመቱ የካቲት 23 በተለይ በአዲስ አበባ በድምቀት ይከበራል፡፡ ይሁን እንጂ ዘንድሮ ለ127ኛ ጊዜ የሚከበረው ይኸው የአደዋ ድል በዓል ከወዲሁ ውዝግቦች ተነስተውበታል፡፡ ከውዝግቦቹ መካከል አንዱ በበዓሉ ዕለት የሚለበሱ የተለያዩ መልዕክት የያዙ ቲሸርቶችን ሽያጭና ስርጭት መግታት ሲሆን፣ በዓሉን የሚዘከሩ መድረኮች ላይ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ምስል ሳይኖር ሌሎች ምስሎች መታየታቸው ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት የአድዋ ክብረ በዓልን የሚያከብሩ ሰዎች ከበዓሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መልዕክቶችና ምስሎችን የያዙ ቲሸርቶችን አሠርተው ይለብሱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዘንድሮው ክብረ በዓል ላይ ቲሸርቶቹን አትመው ለገበያ በሚያቀርቡ የህትምት ቤቶች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ እየደረሰባቸው መሆኑን በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ሰዎች እየገለጹ ነው፡፡ ይህ ተጽዕኖ የሥራ ቦታ ከማሸግ፣ የቲሸርት ህትመት ሲያትሙ የተገኙ ሰዎችን እስከማሰር የደረሰ ሲሆን፣ በተለይ ከትላንትና ጀምሮ ፖሊስ በየማተሚያ ቤቱ እየዞረ ለማተሚያ ቤቶች ማስጠንቂያ ሰጥቷል፡፡ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ተላልፈው ቲሸርት አትመው ለገበያ የሚያቀርቡ ከሆነ ንብረታቸው እንደሚወረስና እነርሱም እንደሚታሰሩ ነጋዴዎች ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት ቁጥጥር ማድረጉን ተከትሎ፣ ቲሸርቶችን በማተም ሥራ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ነጋዴዎች ቲሸርቶችን በድብቅ እያተሙ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ባለፉት ሳምንታት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ማስታወቂያ ሲሰሩ የነበሩ የህትመት ቤቶች ከሰሞኑ የማስታወቂያ ሥራቸውን ማቆማቸውንም ታውቋል። የዘንድሮውን የአድዋ ዓመታዊ ክብረ በዓል በመከላከያ ሚኒስቴር የበላይ አስተባበሪነት የሚከናወን ሲሆን፣ ዝግጅቱ የመከላከያ ምክትል ኢታማዦር ጀነራል አበባው ታደሰ በሰብሳቢነት እንደሚመሩት ተገልጿል፡፡ ጀነራል አበባው የክብረ በዓሉን ዝግጅት አስመለክቶ ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ በበዓሉ ላይ የሚለበሱ ቲሸርቶችን በተመለከተ በሰጡት ሐሳብ የጥላቻ መልዕክት ያዘለ ካልሆነ በቀር ጥበቅ ክልከላ እና ቁጥጥር አይደረግም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ እንደ ጀነራሉ ገለጻ ከሆነ፣ ለበዓሉ የሚለበሱ ቲሸርት ህትመቶች ላይ መንግሥት ወይም አስተባበሪው አካል ቁጥጥር እያደረገ ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ፣ ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በተገናኘ በበዓሉ ላይ ኮከብ የሌለው አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ሕጋዊ መሰረት ባይኖረውም ኅብረተሰቡ ያዘ አልያዘ በሚል ውዝግብ እንደማይኖር መግለጻቸው ተጠቁማል፡፡ ዘንድሮውን የአድዋ ክብረ በዓል የሚዘክሩ መድረኮች ከሰሞኑ የተካሄዱ ሲሆን፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ በተሳተፉበት መድረክ ላይ የአድዋ ድል ጀግና ከሆነው ባልቻ አባ ነፍሶ ጋር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፎቶ መታየቱ ውዝገብ ያስነሳ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ይኸውም ከባልቻ አባ ነፍሶ ጋር በፖስተር ላይ መታየትና በጀግንነት መዘከር ያለባቸው ዳግማዊ አጼ ምኒሊክን ጨምሮ በርካታ የአድዋ ጀግኖች እያሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምን አግባብ በዝክር ፖስተር ላይ ተቀመጡ የሚለው ነው፡፡ ዘገባው የአዲስ ማለዳ ነው።
Source: Link to the Post