በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በየካ አቦዶ የወረዳ 14 አካባቢ ነዋሪዎች ምንም ባልተወያየንበት እና በማናውቀው ሁኔታ በፌደራል ፖሊስ የታጀቡ በርካታ ሰራተኞች መሬታችን እየቆፈሩ አጠር ለማጠ…

በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በየካ አቦዶ የወረዳ 14 አካባቢ ነዋሪዎች ምንም ባልተወያየንበት እና በማናውቀው ሁኔታ በፌደራል ፖሊስ የታጀቡ በርካታ ሰራተኞች መሬታችን እየቆፈሩ አጠር ለማጠር እየተንቀሳቀሱ መሆኑ አሳስቦናል ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ፤ የወረዳ አስተዳዳሪዋ ወ/ሮ ለምለም ዓባይ በበኩላቸው ለልማት ስለሆነ ስጋት አይግባችሁ ባይ ናቸው። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ከአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ የካ አባዶ ከወረዳ 14 ቅሬታቸውን ያቀረቡ ነዋሪዎች እንዳሉት የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ የታጀቡ ከ50 የማያንሱ የቀን ሰራተኞች ከፈረንሳይ አንቆርጫ አካባቢ ጀምረው በየካ አባዶ ኮንዶሚኒየም አድርጎ ማርያም መስመር ድረስ ያለውይይትና ያለእኛ እውቅና መሬታቸውንና አካባቢያቸውን እየቆፈሩት ነው። በግምት ከ4 እስከ 5 ሽህ የሚደርስ ጉድጓድ(ጎሬ) መቆፈሩን ነዋሪዎች ገልፀዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች እነማን ናችሁ፣ ለምንድን ነው መሬታችን የምትቆፍሩት፣ ማን ፈቀደላችሁ የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ቢያነሱም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ታዘን ነው፤ ለልማት ነው የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል። ይሁን እንጅ አጥር እያጠሩ ያሉት “በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መካከል የመለያያ የወሰን አጥር ለማበጀት መሆኑን ሰምተናል ይህ ደግሞ ያለእኛ ፍቃድና ውይይት እንዴት በአፈና መልኩ ይፈፀማል?” በሚል የተበሳጩ የአካባቢው ነዋሪዎች የካቲት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ሆብለው በመውጣት የተቆፈሩ ጉድጓዶችን በሙሉ በድንጋይና በአፈር ደፍነዋል። ከየካ አባዶ ወረዳ 14 ነዋሪዎች መካከል የልማት ቡድን አመራሮች በእለቱ ከወረዳ አስተዳዳሪዋ ወ/ሮ ለምለም ዓባይ ጋር ለመወያየት ሞክረዋል፤ የልማት ጉዳይ መሆኑን ከመግለፅ ያለፈ ዝርዝር መረጃ ሳያጋሩ በትነዋቸዋል። በማግስቱ የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የየካ አባዶ ወረዳ 14 ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ ለምለም ዓባይ የኦሮሞ ማንነት ያላቸውን ብቻ ነጥለው በመሰብሰብ አሳታፊነት የጎደለው ውይይት አድርገዋል ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎች ይወቅሳሉ፣ይከሳሉም። በነበራቸው ውይይትም በአካባቢው ነዋሪ የሆኑና የማህበረሰቡን ጥያቄ ሲደግፉ የነበሩ ኦሮሞዎችን “ለእናንተ ጥቅም ነው፤ በአዲስ አበባ የተወሰደባችሁን መሬት ለማስመለስ ስለሆነ ለምን በእንደዚህ ዓይነት የአመፅ ተግባርን ትተባበራላችሁ? በሚል ስለወቀሷቸው ቀደም ሲል ከነበራቸው አቋም ተመልሰው ማነው የጎሬ ቁፋሮውን የሚቃወመው በሚል የመለየት ስራን የሚያግዙ እንዳሉ አውቀናል” ይላሉ_ቅሬታ አቅራቢዎቹ። ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ “ቤተ ክርስቲያን ሳይቀር ለምን ታሰራላችሁ፣ አማራ ሰፈር ለምን ታስብላላችሁ? እኛ የእናንተን መብት ለማስከበር ስንገባ እናንተ ደግሞ ለምንድን ነው እኛን የማትቀበሉን?” ተብለው አሳታፊነት በጎደለው ስብሰባ የተነገራቸው እንዳሉ መረጃው ደርሷቸዋል። ለነገሩ አስቸኳይ ካልተሰጠው ህዝቡ ባላወቀውና ባልመከረበት ሁኔታ በድብብቆሽ የሚደረግ ልማትም ይባል ወሰን ማካለል ለመቀበል ይቸግረናል፤ አብሶ በዚህ በምርጫ ወቅት ወደ ኦሮሚያ በማካለል መምረጥ እንዳችል የሚደረግ ከሆነ ሌላ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሚፈጥር ሊታወቅ ይገባዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። የአማራ ሚዲያ ማዕከል ያነጋገራቸው በየካ ክፍለ ከተማ የየካ አባዶ(ለሚ ኩራ) ወረዳ 14 ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ ለምለም ዓባይ በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካልም ሆነ ህዝብ ሳያውቅ የሚሰራ አንድም ልማት የለም፤ እኛም ከሚመለከተው አካል ጋር ተወያይተን ነው ከፈረንሳይ አንቆርጫ አካባቢ ጀምረን በየካ አባዶ ኮንዶሚኒየም ድረስ ለፕሮጀክት ጉድጓድ ያስቆፈርነው ሲል አስተባብለዋል። ከህዝብ ጋር ብትወያዩና ግልፅ ቢሆንለት ኖሮ የካቲት 22 ያስቆፈራችሁትን ጉድጓድ በማግስቱ የካቲት 23 በአፈርና በድንጋይ ባልደፈነው ነበር ለተባሉት ወ/ሮ ለምለም ሲመልሱ በእርግጥም ግንዛቤው ያልነበራቸው የተወሰኑ አካላት ያደረጉት ነው፤ ይህን ለማስተካከል ህዝቡን ሰብስበን አወያይተናል ብለዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የተያዘ የልማት ፕሮጀክት እንጅ ወሰን የማካለል ጉዳይ አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል። ህዝብን ከፋፍሎ ማወያየት ለምን አስፈለገ ለተባሉት ብሄርን ለይቸም አላወያየሁም ሲሉ ነው ለተነሳው ቅሬታ ምላሽ የሰጡት። ከየካ አባዶ ወረዳ 14 ቅሬታ አቅራቢዎችና ከወረዳ አስተዳዳሪዋ ወ/ሮ ለምለም ጋር ያደረግነውን ቆይታ በአሚማ የየቱብ አድራሻ ይጠብቁ።

Source: Link to the Post

Leave a Reply