በአዲስ አበባ የ40/60 እና የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት ይካሄዳል

25 ሺህ 491 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች በዕጣ ይተላለፋሉ

አርብ ሀምሌ 1 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ የ3ኛ ዙር የ40/60 እና 14ኛ ዙር የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት ይካሄዳል።

በዚህም ከ2006/07 ጀምሮ ግንባታቸው ሲካሄዱ የቆዩ 25 ሺህ 491 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች በዕጣ ይተላለፋሉ ተብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት በሚመለከት ባሳለፍነው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ፤ በ20/80 ፕሮግራም 18 ሺህ 648 እንዲሁም በ40/60 መርሃ ግብር 6 ሺህ 843 ቤቶች በድምሩ 25 ሺህ 491 ቤቶች ለነዋሪዎች በእጣ እንደሚተላለፉ አስታውቀዋል።

በእጣውም የመንግስት ሰራተኞች 20 በመቶ፣ ሴቶች 30 በመቶ፣ የአካል ጉዳተኞች 5 በመቶ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

በተጨማሪም በ14ኛው ዙር እጣ ብቁ የሚሆኑት የ20/80 ነባር ተመዝጋቢዎች ከ1997 እስከ የካቲት 21 ቀን 2014 ድረስ የቆጠቡና፤ የ40/60 ተመዝጋቢዎች እስከ የካቲት 21 ቀን 2014 ድረስ 40 በመቶ እና ከዚያ በላይ ቁጠባ ያላቸው እንደሚሆኑም ከንቲባዋ አረጋግጠዋል፡፡

በዚህም መሰረት በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 27 ሺህ 195 እና 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም 52 ሺህ 599 ተመዝጋቢዎች፤ በአጠቃላይ 79 ሺህ 794 ተመዝጋቢዎች ለዕጣ ብቁ ሆነው በዚህ ዙር ዕጣ ውስጥ እንዲካተቱ ተደርገዋል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ያስሚን ዋህብረቢ በበኩላቸው፤ ቤቶቹ 97 በመቶ አማካኝ አፈፃፀም ላይ የደረሱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በእጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ጥቅም ላይ የሚውለው ሶፍትዌርም የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያበለፀገውና፤ የፌደራልን ጨምሮ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ታይቶ ይሁንታን ያገኘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም አያት 2፣ ቦሌ በሻሌ፣ ቡልቡላ ሎት የሚገኙ ሲሆኑ፤ በ20/80 በረከት፣ ቦሌ አራብሳ ሳይት 3 ሳይት 5 እና 6 ወታደር፣ የካ ጣፎ፣ ጀሞ ጋራ፣ ጎሮ ስላሴ ፣ ፉሪ ሀና እና ፋኑኤል የሚገኙ መሆናቸውንም ታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖርያ ቤቶቹን እጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት በትላንትናው ዕለት ለማካሄድ ፕሮግራም ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ነገር ግን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጠራው ስብሰባ ምክንያት የእጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓቱን ወደ ዛሬ አርብ ሀምሌ 1 ቀን 2014 ማዘዋወሩን ማስታወቁ ይታወሳል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply