በአገራዊ ምክክሩ ህዝበ ሙስሊሙ በቁጥሩ ልክ ተሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

     በአገራዊ ምክክሩ የሚሳተፈው የሙስሊሙ ቁጥር አናሳ መሆኑን የገለፀው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት  የተሳታፊዎች ልየታ  በድጋሚ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቧል። በሙስሊሙ በኩል የቀረቡ አጀንዳዎች በምክክሩ ውስጥ እንዲካተቱም ጠይቋል።
“የሙስሊሞች ተሳትፎ በሕዝባችን ቁጥር ልክ መሆን አለበት” ያለው ም/ቤቱ”፤ የተሳታፊዎችና የአወያዮች ቁጥር በኮሚሽኑ የአካታችነት መርህ አማካይነት አንዲታይ አመልክቷል።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የበላይ ጠባቂ፣ ለፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በፃፈው ደብዳቤ፤  የሕዝበ ሙስሊሙን የምክክር እጀንዳዎች ለጉባኤው ለማሰማትና ለማብራራት የሚችሉ ተገቢ ቁጥር ያላቸው ሙስሊም ተወካዮች እንዲካተቱ የሚጠይቅ ሃሳብ ከህዝቡ መምጣቱን ገልጿል። በዚህም ምክንያት “ስብጥሩ በፍትሐዊነት እንደገና ይቃኝ” ሲል ጠይቋል።

ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ውጪና ግጭት ባለባቸው የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎችን ሳያካትት፣ በ10 ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለምክክሩ የሚሳተፉ አካላትን ልየታ ቢያካሂድም፣ “የሙስሊሙ ቁጥር አነስተኛ ነው” ብሏል – ጠቅላይ ምክር ቤቱ፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተወካዮች ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ሦስት ሃላፊዎች ጋር  ውይይት ማድረጋቸውም ተነግሯል። “በባለሞያ በተሰጠ መግለጫ ላይም  በተሳታፊና በአወያይ ደረጃ የሙስሊሞችን ተሳትፎ እንዲነገረን ብንጠይቅም፣ ከምክክር ኮሚሽኑ ምላሽ አልተሰጠንም” ሲል ጠቅላይ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡
አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጤነው የጠየቀው ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለኮሚሽኑ የቀረቡ የመስሊሙ አጃንዳዎች እንዲካተቱና ህዝበ ሙስሊሙም በቁጥሩ ልክ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቀርቧል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር እንደሚያስችል የታመነበት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply