በአፋርና ኦሮሞ ብሄረሰብ አዋሳኝ ድንበሮች በተከሰተው ግጭት ከሰው ህይወት መጥፋት በተጨማሪ ንብረት መውደሙ ተገለጸ

በሁለቱ አዋሳኝ ድንበሮች በተነሳው ግጭት በሰዎቸ ላይ የሚደርሰው ሞት ቢቆምም ከ70 በላይ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ፖሊስ መምሪያ ገልጿል፡፡ከድንበር ጋር በተያያዘ በአካባቢው የሚነሳው ግጭት አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በቅርቡ ከ8 ቀናት በላይ የፈጀ ግጭት በአካባቢው ተከስቷል፡፡

ግጭቱን ለማርገብ በስፍራው የሚገኘው አመራር ሰፊ ስራ እየሰራ ሲሆን አሁን ላይ ግድያዎች ቢቆሙም በተለያዩ ቀበሌዎች ላይ ቤትና ንብረትን ማውደም ተግባር መስፋፋቱን የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መሐመድ ያሲን ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

አሐዱም ችግሩን እልባት ለመስጠት በስፍራው ያለው የህግ አካል ምን እየሰራ ነው ሲል የጠየቀ ሲሆን ኮማንደር መሐመድ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ለሚመለከተው አካላት ሪፖርት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቤት ንብረታቸው የተቃጠለባቸው ሰዎች በአንበጣ መንጋ መከሰት ለከፋ ችግር ተጋልጠው የነበሩ መሆናቸው ችግሩን እጥፍ ድርብ ያደርጋል ሲሉ የመምሪያው ኃላፊ አሳሳቢነቱን ተናግረዋል፡፡

ግጭቶቹ መቆማቸውን የገለጹት ኮማንደሩ አሳሳቢ የሆነው ጨለማን ተገን አድርገው ቃጠሎ የሚፈጥሩት ችግር ነው ብለዋል፡፡

**************************************************************************

ዘጋቢ፡ፀጋነሽ ደረጀ

ቀን 22/04/2013

Source: Link to the Post

Leave a Reply