በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመቆጣጠርና ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት እየተሰራ ነው

በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመቆጣጠርና ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 21 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ባለበት ለመቆጣጠርና ወደ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች በመዛመት ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በአሁኑ ወቅት የበረሃ አንበጣው በአፋር ክልል በ26 ወረዳዎችና በምስራቅ አማራ አጎራባች ወረዳዎች እና በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን በሚገኙ በአይሻ፣ አወበሬ እና ሽንሌ ወረዳዎች ዳግም ተከስቷል ነው ያለው ሚኒስቴሩ፡፡

የዘንድሮው የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ እስካሁን በሰብል ላይ ጉዳት ባያደርስም ግጦሽና በቁጥቋጦ ላይ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል ተብሏል፡፡

በዚህም በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ባለበት ለመቆጣጠርና ወደ አማራ፣ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች በመዛመት ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የግብርና ሚኒስቴር ከክልሎች ጋር ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር እና አስፈላጊውን የኬሚካል፣ የተሽከርካሪዎች፣ የአሰሳ ሄሊኮፕተሮችና የመርጫ አውሮፕላኖች እንዲሁም በቂ ባለሙያዎችን በመመደብ ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በመሆን የመቆጣጠር ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡

የበረሃ አንበጣውን ለመከላከል በተደረገው ሁለገብ እንቅስቃሴ ከሰኔ 2011 ጀምሮ በ1 ሚሊየን 307 ሺህ 306 ሄክታር መሬት ላይ አሰሳ ተካሂዶ 528 ሺህ 880 ሄክታር መሬት ላይ መከሰቱን በማረጋገጥ የግጦሽና የእርሻ መሬት ላይ በሰው ኃይል የሚሠራና በመኪና በተጠመደ መርጫ መሳሪያ በአውሮፕላን በመታገዝ የፀረ-ተባይ ኬሚካል ርጭት በማካሄድ እንዲሁም ህዝቡን በማሳተፍ በባህላዊ ዘዴ ጉዳት እንዳያደርስ የመከላከል ስራ ተሰርቷል፡፡

የበረሃ አንበጣው በ2011/12 ዓ.ም ምርት ላይ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ወይም ከዓመቱ ምርት ውስጥ አንድ በመቶ የሚሆን ምርት ላይ ጉዳት ማድረሱን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

The post በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመቆጣጠርና ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት እየተሰራ ነው appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply