
በአፋር ክልል ሱላ በርሃ ከአንድ ዓመት በላይ በአገዛዙ የአፈና እስር የቆዬው እና በርሃብ እና በህክምና ጉድለት በስቃይ ህይወቱ ያለፈውን የጀግናው ፋኖ ውድሰው ይልማ አበበን በድርብርብ ሀዘን የተጎሳቆሉ ጀግና እናትን እንደግፍ፤ ከጎኗ በመሆን የተሰበረ ልቧን እንጠግን፤ የእናትነት ምርቃቷም ይድረሰን! አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ሀምሌ 15/2015 ዓ/ም_አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በብልጽግናው አገዛዝ እና እነ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ እየመራነው ነው በሚሉት አማራ ክልል የስርዓቱ ተልዕኮ ፈጻሚዎች ከግንቦት 2014 ጀምሮ ቢያንስ ከ1,400 በላይ የሚሆኑ አማራነት የመዳኛ መንገዳችን መሆኑን ያቀነቀኑ፣ ፋኖነት፣ አርበኝነት የአማራ ህዝብ ከገጠመው የህልውና አደጋ የመውጫ መንገድ መሆኑን ቀድመው የተረዱ ወጣቶችን በህግ ማስከበር ሽፋን እያፈኑ በተለይም በደቡብ ጎንደር ነፋስ መውጫ እና በምስራቅ ጎጃም የትኖራ ላይ ባሉ ማጎሪያዎች አሰቃቂ ግፍ እና በደል ሲፈጽሙባቸው መቆዬታቸው ይታወቃል። ይሁን እንጅ በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረውን የህዝብ ከፍተኛ ጫናን ተከትሎ ክልሉ ከፌደራል መንግስት ጋር በመሆን አፍነው ለሚያመጡ ተላላኪዎች 600 ብር የውሎ አበል በመክፈል ከእዬ አቅጣጫው የሰበሰቧቸውን የሀገር ባለውለታዎች:_ የመከላከያ ምልስ የፋኖ አባላትን፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ የፖሊስ፣ የሚሊሻ አባላት እና ሲቪሎችን የስርዓቱ አሽከር ባለመሆናቸው፣ በፋኖነታቸው፣ በአርበኝነታቸው እና የነቁ እና የአማራውን የመውጫ መንገድ ቀድመው የተረዱ በመሆናቸው በትንሹ ከ1,400 በላይ የሚሆኑትን በጨለማ እና በሽፍን መኪና በማስገባት ወደ አፋር ክልል መውሰዳቸው ይታወሳል። ከአማራ ክልል ወደ አፋር፣ ከኤርትራ 42 ኪ/ሜትር ርቀት ባለ በርሃማ የሱላ ወታደራዊ ካምፕ የተወሰዱትም ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት ከግንቦት 2014 ዓ/ም ጀምሮ ነበር። አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ከታፈኑት አንደበት ባገኘው መረጃ መሰረት ባለፈው አንድ ዓመት ውድሰው ይልማን ጨምሮ 15 ፋኖዎች በከፍተኛ ሙቀት፣ በርሃብ እና በህክምና እና በመድኃኒት አቅርቦት ችግር ህይወታቸው ሲያልፍ፣ ጠባቂዎች ለማምለጥ ሙከራ ያደረጉ 4 ፋኖዎችን በድብደባ ሲያሰቃዩ እንዲተዋቸው በተማጸኑ ጓዶቻቸው ላይ በመተኮስ ሶስት ሲገድሉ ስምንት አቁስለዋል። በግፍ ከታሰሩት መካከል ግማሽ የሚሆኑት ከብዙ መከራ በኋላ ሲፈቱ ከ720 በላይ የሚሆኑ የአማራ ልጆች የመከላከያ ምልስ የነበሩ ፋኖዎች በጅምላ እያንዳንዳቸው 2፣ 5 እና 6 ዓመታት በርሃ ላይ እንዲቆዩ ተፈርዶባቸዋል። “ወንጀል አልፈጸምንም፤ ፍርዱም ትክክል አይደለም፤ ማሰር አለብን ካላችሁ ደግሞ ወደ አማራ ክልል ማ/ቤቶች አዘዋውሩን” በማለት ቢማጸኑም ሰሚ ጆሮ አላገኙም። የተፈረደባቸው ከተፈቱት የሚለያቸው አንዳች ነገር በሌለበት፣ መደበኛ ክርክር ባልተደረገበት፣ ምስክር ባልተሰማበት፣ የተለዬ ሰነድ ባልቀረበበት፣ ከ720 በላይ የሚሆኑትን ስለ ምን እና በምን ምክንያት ለይተው እንዳስቀሩ ጨካኝ ጸረ አማራ አሳሪዎቹ ብቻ ነው የሚያውቁት። ከወራት የርሃብ እና የህክምና ችግር በኋላ ሀምሌ 12/2015 ከሌሊቱ 9 ሰዓት ላይ ህይወቱ ያለፈው እና እዛው በርሃ ላይ የተቀበረው የጀግናው ፋኖ ውድሰው ይልማ አበበ የስቃይ ሞት፣ በሌሎች ቀሪ ወንድሞቻችን ላይ መደገሙ እንደማይቀር በከፍተኛ ጭንቀት እና መከራ ውስጥ ሆነው የሚናገሩት የግፍ እስረኞችም አሁን ላይ ሟችን ሲቀብሩ ከ7 በላይ የሚሆኑት ክፉኛ የደከሙ መሆናቸውን በማስረዳት ጭምር ነው። መሳሪያ ጠምደው የደከሙ ሰዎችን እየጠበቁ የሚገኙት የአገዛዙ ተልዕኮ ፈጻሚዎችም ሚናቸው መጠበቅ መሆኑን ብቻ በመግለጽ “አርፋችሁ ታሰሩ!” በማለት በማስፈራራት የሚታወቁ ናቸው ተብሏል። በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በወሎ ኮምቦልቻ በኩል ተሰልፎ እያለ እግሩን በጥይት የተመታው ውድሰው ይልማም ከመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ውጭ ድጋፍ የሰጠው የአገዛዙ አካል አልነበረም፤ አንድ እግሩ ሰሎ በክራንች ሲሄድ እያዬው እንኳ ና ለወንበሬ ሙትልኝ እያለ ሲያስገድደው ነው የነበረው። ባለቤታቸው በማረፉ ያለ አባት ውድሰው ይልማን እና ሌሎች ወንድም እና እህቶቹን እንደ እናትና አባት ሆነው የማሳደግ እና የማስተማር ድርብርብ ኃላፊነቱን የወሰዱት ወ/ሮ ስንታዬሁ አዳነ ሞላ በእጅጉ ተፈትነዋል። እስከ አስረኛ ክፍል አስተምረው ውጤት መጣለት ብለው ሲደሰቱ የህወሓት ወራሪ ኃይል አማራ እና አፋር ክልልን በመውረሩ እኔም ለአማራው ወገኔ እና ለሀገሬ እታገላለሁ በሚል ተመዝግቦ በመሄድ እስኪቆስል ድረስ ተጋድሎ ፈጽሟል። በመጨረሻም ወደ ቤተሰብ ተመልሶ መጀመሪያ በዊልቸር ከዛም በክራንች እየተንቀሳቀሰ ባለበት ሁኔታ ሰኔ 7/2014 በአገዛዙ አፈና ተፈጽሞበት፣ ከብዙ መከራ በኋላ ነው አሳዛኙ የስቃዩ ብሎም መጨረሻ ላይ የመሞቱ መርዶ የተሰማው። ከቤተሰብ በተጨማሪ በምስራቅ ጎጃም ዞን ተወልዶ ባደገበት እና በተማረበት በእናርጅ እናውጋ ወረዳ የደብረ ወርቅ ከተማ ነዋሪዎችም አሁን ላይ ወደ እናቱ እና እህት ወንድሞቹ ቤት በማቅናት የሀዘናቸው ተካፋይ በመሆን እያጽናኑ ይገኛሉ። ከምስራቅ ጎጃም ዞን እናርጅ እናውጋ ወረዳ ደብረ ወርቅ ከተማ የሟች ፋኖ ውድሰው ይልማ እናት ወ/ሮ ስንታዬሁ አዳነ ሞላ “ሶስት ዓመት ሙሉ ሲታገል ኖረ” ይላሉ። እግሩን በጥይት ተመቶ ቆስሎ እንደነበር የተናገሩት ወ/ሮ ስንታዬሁ “እግሬን አላስቆርጥም ብሎ በክራንች ከሚንቀሳቀስበት ከዚሁ ከጎጆዬ ላይ አፍነው ሲወስዱት እሪ ብልም ሰሚ አላገኘሁም” ነበር ሲሉ የደረሰውን ከባድ በደል ያስተውሳሉ። “እኛም ጸሎት እናደርጋለን፤ ለአገራችን የሚስማማ፣ መልካም መንግስት እንዲሰጠን” ሲሉ ደሙን አፍሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ ሀገር ባስከበረ፤ እግረ መንገዱንም የአገዛዙን ወንበር ባደላደለ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ልጃቸው ተሰቃይቶ እስኪሞት ድረስ የመታሰሩ ስርዓታዊ ጥላቻ የተሞላበት ጭካኔ ልባቸውን ክፉኛ እንደሰበረው ለመረዳት ተችሏል፤ መልካም መንግስት እናገኝ ዘንድም ትግላቸው በጸሎት መትጋት እንደሆነ ተናግረዋል። የሟች እህት በበኩሏ ውድሰው ሰኔ 7/2014 በደብረ ወርቅ ከተማ ከመኖሪያ ቤቱ ተይዞ ወደ የትኖራ ካምፕ ከተወሰደ በኋላ ለአንድ ወር ታፍኖ ስለመቆዬቱ፤ በኋላም ወደ አፋር ሱላ ወታደራዊ ካምፕ ወስደው ከአንድ ዓመት በላይ ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኝ በማድረግ አስረው በማቆዬት ለሞት እንደዳረጉት አስተውሳለች። “መጀመሪያ በዊልቸር ቀጥሎም በክራንች እየተንቀሳቀሰ የነበረውንና አንድ እግሩ የሰለለውን ወንድሜን ነው እንደ ሽፍታ እና እንደ በዳይ ሰው በማዬት በሽፍን መኪና አፍነው የወሰዱት” ስትል ያችን ክፉ፣ እርጉም፣ ጥቁር የተያዘበትን ቀን ታስተውሳለች። እየተሰቃዬ መሆኑን እየሰማንም በፕሌን አፋር ድረስ ለመሄድ የገንዘብ አቅሙ ስላልነበረን እኛም አልቅሰን ዝም አልን በማለት በጥልቅ ሀዘን ውስጥ በመሆን ተናግራለች። ከሞተው ወንድሟ ጉዳይ አለፍ ስትልም በስቃይ እስር ላይ የሚገኙ ጓደኞቹ “እግዚአብሔር ያጽናችሁ!” ብለው ሲደውሉ “እኛም ያው ነን፤ ጸሎት አድርጉልን” እያሉን በመሆኑ “እባካችሁ የወገን ያለ እንድረስላቸው!” ስትል ተማጽናለች። በተመሳሳይ የሟች ውድሰው ይልማ ወንድምም “ሀዘናቸው የህዝብ ሀዘን” ስለመሆኑ ለአሚማ ገልጧል፤ ከእህቱ ባለቤት ጋር በመሆን ባስላለፉት መልዕክትም በአገዛዙ ድርብርብ በደል ለደረሰባቸው ለወ/ሮ ስንታዬሁ አዳነ ሞላ እንድንደርስላቸው ጠይቀዋል። በአፋር ክልል ሱላ በርሃ ለሚገኙት ቀሪ ወንድሞቻችንም በአስቸኳይ በመድረስ የውድሰው ይልማ እጣፈንታ እንዳይገጥማቸው ወገናዊ እና ሰዋዊ ኃላፊነታችን እንድንወጣ ተማጽነዋል። በመጨረሻም በተወለደ በ21 ዓመቱ በአፋር በርሃ ሱላ ወታደራዊ ካምፕ ታስሮ በስቃይ ህይወቱ ካለፈው ከፋኖ ውድሰው ይልማ አበበ እናት ከወ/ሮ ስንታዬሁ አዳነ ሞላ ጎን በመሆን በሀዘን የተሰበረ ልባቸውን እንድንጠግን፤ እንድንመረቅም ጭምር ወገናዊ ጥሪ ቀርቧል። መደገፍ የምትፈልጉ እና የምትችሉ ወገኖች የሚከተለውን በስማቸው የተከፈተ አካውንት መጠቀም ትችላላችሁ። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተከፈተ አካውንት 1000138850378 ስንታዬሁ አዳነ ሞላ ስንታዬሁ አዳነ:_0961875893 ወንዶሰን ይልማ (የልጃቸው) :_0938291974 (የደገፋችሁ በውስጥ ብታሳውቁን) አሚማ ከሟች ፋኖ ውድሰው ይልማ እናቱ፣ እህቱ፣ ወንድሙ እና ከእህቱ ባለቤት ጋር ከሰሞኑ ያደረገውን ቆይታ በሚከተለው ሊንክ ገብታችሁ መከታተል ትችላላችሁ:_ https://youtu.be/L1DyTyTLFs8
Source: Link to the Post