በኡኬ ቀርሳ በኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን እና በተባባሪዎቹ በግፍ ከተጨፈጨፉት ከ50 በላይ አማራዎች መካከል የ7ቱን አስከሬን ብቻ ስለማንሳታቸው ነዋሪዎች ተናገሩ፤ የሌሎቹን አስከሬን ለማንሳት…

በኡኬ ቀርሳ በኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን እና በተባባሪዎቹ በግፍ ከተጨፈጨፉት ከ50 በላይ አማራዎች መካከል የ7ቱን አስከሬን ብቻ ስለማንሳታቸው ነዋሪዎች ተናገሩ፤ የሌሎቹን አስከሬን ለማንሳት ከሽብር ቡድኑ በተጨማሪ በልዩ ኃይሉ እንጠቃለን በሚል ጊዜ አላገኘንም ብለዋል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጳጉሜ 5 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በምስራቅ ወለጋ ዞን ጉቶ ጊዳ ወረዳ ኡኬ ቀርሳ በአሸባሪ ኦነግ ሸኔ እና የዘር ማጥፋት ተባባሪዎቹ በማንነታቸው ተመርጠው ወጣት፣አዛውንት፣ ህጻን፣ሴት፣ አቅመ ደካማ፣ቄስ፣ ሼህ ሳይል በአሰቃቂ መልኩ በየቤታቸውና ከቤታቸው ውጭ ጭምር ከተጨፈጨፉት ከ50 በላይ አማራዎች መካከል:_ በኡኬ ቀርሳ የነበረ የዐይን እማኝ እንደሚለው 8ቱ በአንድ ቤት ውስጥ እና በር ላይ በጥይትና በስለት የተገደሉ ናቸው፤ 6 ሜዳ ላይ የወደቁ እና አስከሬናቸው ያልተነሳ መሆኑንም ገልጧል። 7 የሚሆኑ የሟቾችን አስከሬን አንስተው ወደ ሌላ አካባቢ ለመውሰድ መቻላቸውን የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ምንጮች አረጋግጠዋል። በአጠቃላይ ከ50 በላይ አማራዎች በቡድን መሳሪያ ጭምር በመታገዝ በጥይትና በስለት ጳጉሜ 4/2014 ከንጋቱ 12 ሰዓት እስከ ቀኑ 8:30 በግፍ እና በገፍ በሽብር ቡድኑ ስለመጨፍጨፋቸው የሚናገሩት ምንጮች የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ከቀኑ 8:30 ሰዓት በኋላ ኡኬ ቀርሳ ስለመድረሱ ተናግረዋል። አስከሬን በማንሳት ላይ የነበሩ አማራዎችም ከሽብር ቡድኑ በተጨማሪ የልዩ ኃይሉ ሁኔታ አላማረንም፤ ያጠቃናል በሚል 7 አስከሬን ብቻ ይዘው መውጣታቸውን ገልጸዋል። ልዩ ኃይሎቹ ንጋት ላይ በነበረው ተኩስ ያለበቂ ውጊያ የቡድን መሳሪያቸውን ጭምር ጥለው ወደ መንደር 10 መሸሻቸው ተገልጧል። የኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድኑ በቆይታው ፖሊስ ጣቢያውን በማቃጠል 3 ባንኮችን ስለመዝረፉ እና ስለመሰባበሩ ተነግሯል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply