You are currently viewing በኢትዮጵያ ለአንድ ሳምንት የታሰረው ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ ተለቀቀ

በኢትዮጵያ ለአንድ ሳምንት የታሰረው ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ ተለቀቀ

ላለፈው አንድ ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ በእስር ላይ የቆየው ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ፤ ዛሬ ሐሙስ ከቀኑ 10 ሰዓት ገደማ ከእስር መለቀቁን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። “አፍሪካ ኢንተለጀንስ” ለተሰኘው የዜና ድረ ገጽ ዘጋቢ የሆነው አንቷን፤ ዛሬ እኩለ ለሊት ገደማ ኢትዮጵያን ለቅቆ ወደ ሀገሩ መመለሱን ምንጮቹ ተናግረዋል።

ጋዜጠኛው ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ አዲስ አበባ የመጣው፤ ዓመታዊውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ለመዘገብ እንዲሁም ኢትዮጵያን የተመለከቱ ዘገባዎች ለማዘጋጀት እንደነበር የሚሰራበት መገናኛ ብዙሃን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። አንቷን የሲቪል ልብስ በለበሱ የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋለው፤ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 14፤ 2016 መሆኑን “ኢንዲጎ ፐብሊኬሽንስ” የተሰኘው የድረገጹ አሳታሚ ድርጅት መግለጹ ይታወሳል። 

ጋዜጠኛው የተያዘው፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር ከሆኑት አቶ በቴ ኡርጌሳ ጋር በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል ቃለ መጠየቅ እያደረገ በነበረበት ወቅት መሆኑን ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (CPJ) አስታውቆ ነበር። አንቷን እና በቴ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ፤ ቦሌ ሩዋንዳ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን እንዲሁም ባለፈው ቅዳሜ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ሲፒጄ በመግለጫው አመልክቷል።

ፖሊስ ፈረንሳዊውን ጋዜጠኛ ፍርድ ቤት ባቀረበበት ወቅት፤ “በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሁከት ለማስነሳት ሲንቀሳቀስ መያዙን” መግለጹን በሲፒጄ መግለጫ ተጠቅሷል። አንቷን ድርጊቱን ለመፈጸም ተንቀሳቅሷል የተባለው፤ “ከፋኖ እና ከኦነግ ሸኔ ጋር በመተባበር” እንደሆነ መገለጹንም ሲፒጄ አመልክቷል። ጋዜጠኛው በዋስ ተፈትቶ ጉዳዩን በውጭ እንዲከታተል በጠበቃው በኩል የቀረበው ጥያቄ፤ በፖሊስ በኩል ተቀባይነት እንዳላገኘ መግለጫው አክሏል። 

ሌሎች አባሪ ተጠርጣሪዎች ለመያዝ እና በጋዜጠኛው የሞባይል ስልክ ላይ ምርመራ ለማድረግ፤ ፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጡት ለፍርድ ቤቱ ማመልከቱን ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ ተናግረዋል። ፖሊስ ከጠየቃቸው የምርመራ ቀናት ውስጥ በፍርድ ቤቱ የተፈቀዱለት ስድስት ቀናት ብቻ በመሆኑ፤ ጋዜጠኛው በነገው ዕለት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቶት ነበር።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ በትላንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ አንቷን በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው “ከተሰጠው ፍቃድ” እና ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት “ዋነኛ ዓላማ ውጪ” “በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ መረጃ ሲያሰባስብ” በመቆየቱ እንደሆነ አስታውቀው ነበር። አንቷን ፍቃድ ያገኘው የ37ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ለመዘገብ እንደሆነ ሚኒስትር ዲኤታዋ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።  

“ግለሰቡ ወደ አዲስ አበባ ከገባበት ቀን ጀምሮ ከመጣበት ዓላማ ፍጹም ተቃራኒ የሆኑ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን የሚያሳዩ መረጃዎች ተገኝተዋል” ያሉት ሰላማዊት፤ “ወደ አንድ ሀገር ከገቡበት ዓላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ መገኘት፤ ለተቀባይ ሀገር በተለይ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት የሆኑ ጉዳዮች ላይ ተሰማርቶ መገኘት ወንጀል መሆኑ ይታወቃል” በማለት ጋዜጠኛው የተጠረጠረበትን ጉዳይ አስረድተዋል።  አንቷን “የኢትዮጵያን የውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ሲሞክር” እንደነበርም አክለዋል። 

“[ጋዜጠኛው] ምንም እንኳ የመጣበት ዓላማ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ዘገባ ለመስራት ቢሆንም፤ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎችን አመራሮችን እና አባላትን ሲያነጋግር [ነበር]። ከዚያ ባሻገር የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እና ሌሎችም ከሀገር ውስጥ የፖለቲካ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ የሚያስባቸው አካላት ጋር በመገናኘት መረጃዎችን ሲያሰባስብ መቆየቱን ለመገንዘብ ተችሏል” ሲሉም ሚኒስቴር ዲኤታዋ አብራርተዋል። 

“እንደሚታወቀው ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ዘገባ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ፤ ከመጣበት ዓላማ ውጪ መስራት ህገ ወጥ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ደግሞ በየትኛውም ዓለም ያለ ህግ ነው። በተለይ ደግሞ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን የሚያዘጋጁ፣ ትልልቅ የዲፕሎማሲ ሁነቶችን የሚያዘጋጁ ሀገራት በግልጽ የሚያስቀመጡት ህግ ነው” ብለዋል ሰላማዊት በትላንቱ መግለጫቸው። 

“ወደ አንድ ሀገር ከገቡበት ዓላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ መገኘት፤ ለተቀባይ ሀገር በተለይ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት የሆኑ ጉዳዮች ላይ ተሰማርቶ መገኘት ወንጀል መሆኑ ይታወቃል”

ሰላማዊት ካሳ፤ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ

ግለሰቡ በህግ ጥላ ስር እንዲሆን የተደረገው በዚህ ተግባሩ ተጠርጥሮ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዲኤታዋ፤ “ከሙያው” አሊያም “ከዜግነቱ” ጋር ጉዳዩን ማገናኘት “የተሳሳተ” መሆኑን አስረድተዋል። ጉዳዩ “በፍርድ ቤት እየታየ ያለ” መሆኑን የጠቆሙት ሰላማዊት፤ ከዚሁ ጋር የተያያዙ ተጨማሪ መረጃዎች ሲወጡ ለህዝብ እንደሚያሳውቁ ቃል ገብተው ነበር። የአንቷንን ከእስር መለቀቅ በተመለከተ፤ በእርሳቸውም ሆነ በመስሪያ ቤታቸው በኩሉ እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።  

ሆኖም የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች፤ ፈረንሳዩ ጋዜጠኛ “በምን ሁኔታ ከእስር እንደተለቀቀ” በቀጣይ ቀናት ከራሱ ወገን መረጃዎች ሊወጡ እንደሚችሉ ጥቆማ ሰጥተዋል። ከእስር የተለቀቀው ጋዜጠኛ ዛሬ ለሊት ወደሚኖርበት ከተማ ፓሪስ ቢመለስም፤ አብረው የታሰሩት የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር ግን አሁንም በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ እንደሚገኙ ለእርሳቸው ቅርብ የሆኑ ሰዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ በቴን ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት እንደጎበኟቸው የገለጹት እነዚሁ የቅርብ ሰዎች፤ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኛው በተሰጣቸው ቀነ ቀጠሮ መሰረት “በነገው ዕለት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)    

Source: Link to the Post

Leave a Reply