በኢትዮጵያ ለ5ተኛ ጊዜ አለም አቀፍ የአግሮፉድ እና ፕላስት ፕሪንትፓክ የንግድ መድረክ ከሰኔ 1 እሰከ 3 ቀን 2015 ዓም ድረስ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ሊካሄድ መሆኑ ተገልጿል።
በጀርመኑ የንግድ ትርዒት ስፔሺያሊስት ፌርትሬድ መሴ እና በኢትየጵያው ፕራና ኢቨንትስ የጋራ ትብብር የሚዘጋጀው 5ተኛው አለምአቀፍ የአግሮፉድ እና ፕላስት ፕሪንትፓክ የንግድ መድረክ አስመልክቶ ዛሬ በስካይላይት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
በመግለጫውም የግብርና እና የኢንደስትሪ ሚኒስቴር ኋላፊዎች ፣ ተሳታፊዎች የንግድ ዲፕሎማቶች እና አጋር ተቋማት ተገኝተዋል።
በንግድ መድረኩም ከ16 ሀገራት የተውጣጡ ከ130 በላይ ኩባንያዎች እና ከ3 ሺህ በላይ የንግድ ጎብኚዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡
በ2015ቱ የአግሮፉድ የንግድ ትርኢት ተሳታፊ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ የሚስማሙ የግብርና፣ምግብ ማቀነባበሪያ፣ የምግብ ግብዓት ንጥረ ነገሮች፣ፕላስቲክ፣ህትመት እና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎች እና ሌሎችም ውጤቶች ይዘው እንደሚቀርቡ በመግለጫው ተመላክቷል።
ከቻይና፣ከጀርመን፣ከህንድ፣ከጣሊያን፣ከደቡብ ኮሪያ፣ከኩዌት እና ከቱርክ የተውጣጡ ኩባንያዎች፣ በዚህ የንግድ መድረክ ላይ ተሳታፊ መሆናቸው ተጠቁሟል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ግብርና በዓመት 9 በመቶ አድጓል፣ይህም በዋጋ ሲታይ 36 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከ64 ሚሊዮን ዩሮ እስከ 171 ሚሊዮን ዩሮ የሚደርስ የምግብ እና መጠጥ ማቀነባበሪያ እና የማሸጊያ ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ በማስግባት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ትላልቅ አስምጪዎች አንዷ መሆኗን ገልጿል፡፡
ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ በ2050 ወደ 200 ሚሊዮን እንደሚያድግ የሚጠበቅ ሲሆን በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ትልቁ የምግብ ገበያ እንደምትሆን ቅድመ ትንበያ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በዚህም በምግብ እና መጠጥ ዘርፍ የሚወጣው ወጪ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ ሲሆን የምግብ እና መጠጥ ምርት በኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቁ ክፍል ሆኗል ነው የተባለው።
በ1984 የተቋቋመው ፌርትሬድ በዓለምዓቀፍ የአግሮፉድ እና ፕላስትፕሪንትፓክ የንግድ ትርዒቶችን በአፍሪካ እና በመካከለኛዉ ምስራቅ ለረዥም ዓመታት በማዘጋጀት የሚታወቅ ሲሆን ፕራና ኢቨንትስ እንዲሁ በሃገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ኩነቶችን በማዘጋጀት ይታወቃል፡፡
በእሌኒ ግዛቸው
ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም
Source: Link to the Post