
በኢትዮጵያ ሴቶች በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና ፖለቲካዊ ውሳኔ ሰጭነት ውስጥ በእኩልነት እንዲሳተፉ ባለመደረጉ ምክንያት ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ስለመዳረጋቸው ኢሰመጉ ገለጸ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ የካቲት 29/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል። ኢሰመጉ ሲቀጥል ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በአውሮፓ እና በአሜሪካ በሚገኙ አገራት በነበሩ የሴቶች እንቅስቃሴዎች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1911 ጀምሮ በአለም አቀፍ ሁኔታ ሲከበር የቆየ በዓል መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በያዝነው ዓመትም በአለም ደረጃ ለ112ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን ይህ በዓል መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሁን አስካለንበት ጊዜ ድረስ በርካታ የታሪክ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈ መሆኑን ኢሰመጉ አውስቷል፡፡ ይህ በዓል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1975 ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት አማካኝነት በደማቁ ሲከበር ቆይቷል፡፡ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በየዓመቱ የተለያዩ መሪ ቃልችን በመያዝ የሚከበር ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ “Embracing Equality” “እኩልነትን መቀበል” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን በሀገራችንም ኢትዮጵያ ደግሞ ‹‹እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ›› በሚል መሪ ቃል ለ47ኛ ጊዜ መከበሩ ተገልጧል፡፡ የሴቶች መብቶች አሁናዊ ሁኔታ በአገራችን ኢትዮጵያ በያዝነው 2015 ዓ.ም እንዱሁም ባሳለፍነው 2014 ዓ.ም ዘርፈ ብዙ የሆኑ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በሴቶች ሊይ ስለመፈጸማቸው ኢሰመጉ በመግለጫው ጠቅሷል። ሴቶች በመኖሪያ ቤታቸው፣ በሚማሩበት ትምህርት ቤት፣ በመስሪያ ቤታቸው፣ በመኖሪያ አካባቢያቸው እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ለተለያዩ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲሁም ለወሲባዊ ጥቃቶች ተጋልጠዋል ነው ያለው፡፡ ይህ ጥቃት የሴቶችን ዘር፣ ሀይማኖት፣ቋንቋ፣ አመለካከት እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችን ሳይለይ በየትኛውም እድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሴቶች ላይ ተፈጽሟል ብሏል፡፡ ሴቶች ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች በመሆናቸው ተገቢው የሆነ ጥበቃ እና ከለላ ሳይደረግላቸው በመቅረቱ ለበርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋልጠዋል ሲል አክሏል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በሚነሱ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ተፈናቅለዋል፣ በረሀብ እንዲሁም በተደጋጋሚ በሚነሱ ድርቆች ምክንያት በርካታ ሴቶች ልጆቻቸውን ጨምሮ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል ብሏል ኢሰመጉ በመግለጫው። ሴቶች በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በእኩልነት እንዲሳተፉ ባለመደረጉ ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች በኢኮኖሚያዊ ጥገኝነታቸው ምክንያት ለተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋላጭ እንዲሆኑ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ድምጻቸውን አውጥተው ለመብታቸው እንዳይታገሉ ከፍተኛ ተጽእኖን ፈጥሯል ሲል አክሏል፡፡ በተጨማሪም በአገራችን ኢትዮጵያ የሴቶች የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ሌሎችም መስኮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ መሻሻልን ያሳየ ቢሆንም አሁንም ድረስ ሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ አነስተኛ ነው ብሎታል።
Source: Link to the Post