
በኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት ከ4 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸው ተገለጸ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት ከአራት ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡ እንደ ድርጅቱ ገለጻ፤ ድርቅ ክፉኛ ባጠቃው የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ከ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚልቁ የቤት እንስሳቶች አልቀዋል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ከ4 ሚሊዮን በላይ እንስሳት ሲሞቱ፣ 3 ሚሊዮን የቤት እንስሳት ከሶማሊያ እና 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ገደማ የቤት እንስሳት ከኬንያ ሞተዋል ተብሏል፡፡ የዓለም የምግብ እና የነዳጅ አቅርቦት በማይክሮ ፋይናንስ ቀውስ የተነሳ ችግር ውስጥ መግባቱን ያነሳው ድርጅቱ፣ በአፍሪካ ቀንድ ከመደበኛው ወጣ ያለ የምግብ ዋጋ መናር እና ድርቁ ያስከተለው አደጋ ችግሩን የበለጠ እንዳባባሰው ጠቅሷል፡፡ የእንስሳት ሞት በተለይ በሕጻናት እድገት ላይ አሉታዊ ጫና አለው የተባለ ሲሆን፣ የወተት እጥረት ውሎ አድሮ የአመጋገብ ችግር እንደሚፈጥር ተመላክቷል፡፡ በሦስቱ አገራት ብቻ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ላልተመጣጠን ምግብ ችግር እንደተጋለጡ እና በዚህ የተነሳ 3 ነጥብ 6 የሚጠጉ ታዳጊዎች ትምህርት ለማቋረጥ መገደዳቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጠቁሟል፡፡ የድርቁ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ በሰው እና በእንስሳት ላይ የሚደርሰው ችግር እየሰፋ ይሄዳል ያለው ድርጅቱ፣ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ብቻ በቀጠናው 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ለሚደርሱ የድርቅ ተጎጅዎች አስቸኳይ ድጋፍ ለማድረግ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ያስፈልገኛል ብሏል ሲል አዲስ ማለዳ አጋርቷል።
Source: Link to the Post