በኢትዮጵያ በጎርፍ አደጋ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሠዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸኢትዮጵያ ካሏት ሦስት ወቅቶች ውስጥ አንዱ የሆነውና አራት ወራትን የሚይዘው የበል…

በኢትዮጵያ በጎርፍ አደጋ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሠዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ

ኢትዮጵያ ካሏት ሦስት ወቅቶች ውስጥ አንዱ የሆነውና አራት ወራትን የሚይዘው የበልግ ወቅት በደቡብ አጋማሽ ለሚገኙ የአገሪቱ አካባቢዎች ዋነኛ የዝናብ ወቅት ነው።

ከየካቲት እስከ ግንቦት ያሉትን ወራቶችን በሚሸፍነው የበልግ ወቅት ለሶማሌ፣ ጉጂ፣ ቦረና፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ለደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች 55 በመቶ የዝናብ ስርጭታቸውን ያስገኛሉ።

የበልግ ወቅት ለምስራቅና ደቡብ ትግራይ፣ ለሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች፣ ለአማራና ኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞኖች፣ እንዲሁም አዲስ አበባን ጨምሮ ለመካከለኛው የአገሪቱ አካባቢ፣ ለምስራቅ አካባቢዎች (ሀረርና ድሬዳዋ) ሁለተኛ የዝናብ ወቅት ተደርጎ ይወሰዳል።

የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የ2016 ዓ.ም. የበልግ ወቅት በተለይም ዋነኛና ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖራቸው ትንበያ አውጥቷል።

ባለፉት ሳምንታት ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በደረሱ የጎርፍ አደጋዎች የሠው ሕይወት እልፈትና ለንብረት ጉዳት ደርሷል። በአዲስ አበባ በደረሰው አደጋ አራት ሰዎች በጎርፍ ተወስደው ህይወታቸውን ማለፉን የአዲስ አበባ ከተማ የእሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለቢቢሲ አረጋግጧል።

በሳምንቱ መገባደጃ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀላባ ዞን በደረሰ የጎርፍ አደጋ አምስት ሠዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply