በኢትዮጵያ በ2023 በወባ በሽታ ሳቢያ 527 ሰዎች መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ 

በኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2023 ዓመት፤ አራት ሚሊዮን ገደማ የወባ በሽታ “ኬዞች” መመዝገባቸውን እና 527 በበሽታው ሳቢያ መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አስታውቋል። ከታህሳስ የመጨረሻ ሳምንት እስከ ጥር አጋማሽ ብቻ 84 ሰዎች በበሽታው ህይወታቸውን ማጣታቸውን ድርጅቱ ገልጿል።

የዓለም ጤና ድርጅት ይህን ያስታወቀው፤ በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ወር የነበረውን የጤና ሁኔታ በተመለከተ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው ሪፖርት ነው። ሪፖርቱ ከወባ በሽታ ስርጭት በተጨማሪ በተለያዩ ቦታዎች የተከሰቱትን የኩፍኝ እና የኮሌራ ወረርሽኞችን የዳሰሰ ነው። ባለፉት ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ የወባ በሽታ በምርመራ የተረጋገጠባቸው ወረዳዎች ብዛት በ339 መጨመሩ በሪፖርት ተጠቅሷል።  

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከተመዘገቡ የወባ በሽታ “ኬዞች” ውስጥ 328,881 የሚሆኑት፤ ከዚህ ቀደም በሽታው ባልነበረባቸው ሰዎች ላይ በተደረገ በምርመራ የተገኙ መሆናቸው ሪፖርቱ ገልጿል። ከእነዚህ አዲስ የበሽታው “ኬዞች” መካከል 35 በመቶው የተመዘገቡት በኦሮሚያ ክልል መሆኑን ሪፖርቱ አስፍሯል። የአማራ ክልል 21 በመቶ አዲስ የበሽታውን “ኬዞች” በማስመዝገብ በሁለተኛነት ሲከተል፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በበኩሉ በ12 በመቶ ኬዞች ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ሪፖርቱ አመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)  

Source: Link to the Post

Leave a Reply