በኢትዮጵያ ባለፈው ወር ብቻ 764 ሰዎች በወባ በሽታ ሳቢያ መሞታቸውን የመንግስታቱ ድርጅት አስታወቀ

በኢትዮጵያ ባለፈው የካቲት ወር ብቻ  764 ሰዎች በወባ በሽታ ተጠቅተው መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (OCHA) ገለጸ። የሟቾቹ ቁጥር በጥር ወር ከተመዘገበው የ25 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ጽህፈት ቤቱ ትላንት ሰኞ መጋቢት 16፤ 2016 የሁኔታዎች ግምገማ ሪፖርቱ አስታውቋል።

የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ በዚሁ ሪፖርቱ፤ በኢትዮጵያ በወባ በሽታ መያዛቸው ሪፖርት የተደረጉ ሰዎች ቁጥር 5.2 ሚሊዮን መድረሱን ይፋ አድርጓል። በኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2023 ዓመት ብቻ፤ አራት ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸው ሪፖርት መደረጉን የዓለም ጤና ድርጅት ከአንድ ወር በፊት ባወጣው መረጃ አመልክቶ ነበር። 

ድርጅቱ በዚሁ መረጃው፤ ከታህሳስ የመጨረሻ ሳምንት እስከ ጥር አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ 84 ሰዎች በወባ በሽታ ህይወታቸውን ማጣታቸውን መግለጹ ይታወሳል። የትላንቱ የUN OCHA ሪፖርት በበኩሉ፤ በጥር ወር ብቻ በወባ በሽታ ሳቢያ የተመዘገበው የሞት ብዛት 611 መድረሱን ጠቁሟል። 

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት፤ በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ክልሎች እየተመዘገበ ያለው የወባ በሽታ ተጠቂዎች ቁጥር “በአስቸኳይ ጊዜ ከሚጠበቀው ቁጥር በላይ” መሆኑን በሪፖርቱ ጠቅሷል። ከበሽታው ተጠቂዎች ውስጥ አብዛኞቹ የተመዘገቡት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች መሆኑን ሪፖርቱ ዘርዝሯል።

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመከላከል አጋር ድርጅቶች ለመንግስት በተለያየ መልኩ ድጋፍ ቢያደርጉም፤ ጥረቱ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል። ለበሽታው የመጋለጥ ከፍተኛ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦች ዘንድ የሚስተዋለው “በቂ ያልሆነ የአጎበር አጠቃቀም” በሪፖርቱ በተግዳሮትነት ተነስቷል። 

በማህበረሰብ ደረጃ ያለው የወባ በሽታን “መከላከል እና መቆጣጠር” ደካማ መሆን፤ ለችግሩ “ውጤታማ የሆነ ምላሽ” ለመስጠት እንቅፋት መሆኑም በሪፖርቱ ተነስቷል። የአጋር ድርጅቶች ተሳትፎ ውስንነት እና በበሽታው ከተጠቁ አካባቢዎች የሚሰበሰበው የመረጃ ጥራት ዝቅተኛነት ሌሎቹ በእንቅፋትነት የተቀመጡ ምክንያቶች ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)   

Source: Link to the Post

Leave a Reply