በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የማስታወቂያ ድርጅቶች አውደ ርዕይ ተጀመረ፡፡እየተዳከመ የመጣውን የህትመት ኢንደስትሪ ለመታደግ በሚል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የማስታወቂያ ድርጅቶች አው…

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የማስታወቂያ ድርጅቶች አውደ ርዕይ ተጀመረ፡፡

እየተዳከመ የመጣውን የህትመት ኢንደስትሪ ለመታደግ በሚል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የማስታወቂያ ድርጅቶች አውደርዕይ ተጀምሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለ6 አመታት ተቋርጦ የቆየው እና የማስታወቂያ ድርጅቶችን የሚያሳትፈው አፍሪ ፕሪንት እና ፓኬጂንግ ኤክስፖም ለ7ተኛ ጊዜ መካሄድ ጀምሯል፡፡

አውደ ርዕዩ ለሶስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የወረቀት ህትመት እና ማሸጊያ ቴክኖሎጂ፤የግብዓት እጥረቶች እና መፍትሄዎች ላይ ወይይት ይደረጋልም ተብሏል፡፡

በውይይቱም ከ3 ሺህ በላይ የንግድ ጎብኚዎች ከአውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች ጋር ጠቃሚ የሆነ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የፕራና ኤቨንትስ ማኔጂንግ ዳይርክትር አቶ ነብዩ ለማ ተናግረዋል፡፡

በሃገሪቱ ይህ ኤክስፖ መካሄዱ ተሳታፊ ኩባንያዎች ደንበኞች ሊሆኑ ከሚችሉ ገዢዎች ጋር ለመገናኘት እንዲሁም ንግዳቸውን ወደፊት ለማራመድ ጥሩ መድረክ እንደሚሆን አቶ ነብዩ ገልጸዋል፡፡

ሃገሪቱ ከአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2016 እስከ 2020 በነበሩት አምስት አመታት ውስጥ የህትመት እና ወረቀት ቴክኖሎጂ ከ14 በመቶ በላይ እደገት ማሳየቷን አንስተዋል፡፡

በነዚህ አመታት በምስራቅ እና በመካከለኛው አፍሪካም ታላቋ እና ፈጣኗ የማሸጊያ ቴክኖሎጂ አስመጪ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ዛሬ ላይ የህትመት ግብዓቶች እጥረት እና ትውለዱ የማንበብ ልማዱን ወደ ማህበራዊ ሚዲያው በመቀየሩ፣ ኢንደስትሪውን ማዳከሙን ተከትሎ አንዳንድ የህትመት ሚዲያ አካላትም ከስራው ውጪ እየሆኑ መጥተዋል ተብሏል፡፡

በመሆኑም በሃገሪቱ የወረቀት ህትመት ቴክኖሎጂ እንዳይጠፋ እና በሃገሪቱ ያለውን የህትመት እና የማሸጊያ ኢንደስትሪ ፍጥነት እንዳይገታው ስጋት መደቀኑ ነው የተገለጸው፡፡

ይህ እንዳይፈጠር ታዲያ በሃገር ውስጥ የህትመት ግብዓቶችን የማምረት አዋጭነትን የሚያረጋግጥ ጥናት እየተሰራ መሆኑን የፕራና ኤቨንትስ ማኔጂንግ ዳይርክትር አቶ ነብዩ ለማ ገልጸዋል፡፡

በመሳይ ገ/መድህን
ታህሳስ 11 ቀን 2015 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply