በኢትዮጵያ የዘር ፍጅት ወንጀል እየተፈፀመ ያለው በመንግስት የተደራጀ ኃይል ስላለ ነው  ሲል ባልደራስ – መኢአድ  ከሰሰ፡፡

ጥምረቱ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልከቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡ በመተከል፣ በወለጋ፣ በሰገን አካባቢዎች እየተፈፀመ ያለውን የዘር ፍጅት አጥብቀን እናወግዛለን በሚል የወጣው መግለጫ መንግስትን በፅኑ ይተቻል፡፡

በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት እየተገደሉ ነው፡፡ ግልፅ የሆነ የዘር ፍጅት ወንጀል እየተፈፀመ ነው ሲል ጥምረቱ ወቅሷል፡፡ ለአሐዱ የተላከው የጥምረቱ መግለጫ የአማራ ተወላጆች በወለጋ፣ በጉራፈርዳ፣ በቤንሻንጉልና በሌሎች አካባቢዎች በማንነታቸው ብቻ ለዘር ፍጅት እየተዳረጉ ነው ብሏል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ ሌላው የዘር ፍጅት የሚካሄድበት አካባቢ ደግሞ በሰገን ሕዝብ አካባቢ ነው ሲልም ጠቁሟል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ የጉማይዴ ነዋሪዎችና የኩስሜ ብሔረሰብ አባላት አካባቢ ወገኖችም እያለቁ ነው ሲል ወንጅሏል፡፡ በቁጥሩ አነስተኛ የሆኑትና 40 ሺህ የኩስሜ ብሔረሰብ ዜጎች በአነሷቸው የመልካም አስተዳደር እና የንፁህ ውሃ አገልግሎት ጥያቄዎች ምክንያት ለዕልቂት ተዳርገዋል ሲል ባልደራስ-መኢአድ ጥምረት አስታውቋል፡፡

የኩስሜ ብሔረሰብ አስተዳደር ካሉት 9 አስተዳደር ቀጣናዎች መካከል በ7ቱ ቀጣናዎች ከፍተኛ የሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት የደረሰ ሲሆን በተለይ ቀጣና 1 ሙሉ በሙሉ ወድሞ የኩስሜ ብሔር አባላት ተሰደድዋልም ተብሏል፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆንና ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሲፈፀም የፌደራል መንግስትም ሆነ የክልሉ መንግስት ትኩረት አልሰጡትም ሲልም ነቅፏል፡፡ በዚሁ በሰገን ሕዝቦች አካባቢ የጉማይዴ ሕዝብ የማያባራ የዘር ፍጅት ወንጀል እየተፈፀመበት ነውም ሲል ገልጿል፡፡መንግስት ለዚህ ሕዝብ ሰላምና ፀጥታ መከታ መሆን አለመቻለም ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን የጎዳው በጥቃቱ የመንግስት ባለሥልጣናት ቀጥተኛ እጅ መኖሩ ነውም ሲል ወንጅሏል፡፡ ይህ ሕዝብ የሚደርስበት ግፍ የማያባራው ጥቃቱ በመንግስት የተደራጀ ኃይል እየተፈፀመ በመሆኑ ነው ሲልም በመግለጫው ከስሷል፡፡

****************************************************************************

ዘጋቢ፡ዩሐንስ አሰፋ

ቀን 21/04/2013

 

Source: Link to the Post

Leave a Reply