በኢትዮጵያ የዲጂታል ግብይትን ማስፋፋት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2014 ኢትዮ ቴሌኮም እና ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳዳር ከሰባት ከተሞች ጋር ስምምነት አደረጉ፡፡ ተቋማቱ ስምምነቱን የፈጸሙት ከክልሎቹ የውሀና ፍሳሽ ባለስልጣኖች ጋር ሲሆን ስምምነቱም የደንበኞችን ክፍያ በቴሌ ብር ማዘመን የሚያስችል ነው፡፡ በስምምነቱ የተካተቱት ከተሞች ሐረሪ፣ ባሕር ዳር፣ ፍኖተሰላም፣ እንጅባራ፣ ደሴና ኮምቦልቻ መሆናቸውን የባልደረባችን ባምላክ ወርቁ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በተጠቀሱት ከተሞች የሚገኙ የውሀ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያቸውን በቴሌ ብር መፈፀም መቻላቸው ከአሁን ቀደም የሚደርስባቸውን እንግልት ከመቀነስ ባሻገር ጊዜያቸውን ይቆጥብላቸዋል ነው የተባለው፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት የውሀ አገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤቶች በተቀናጀ ደራሽ የክፍያ ስርዓት አማካኝነት የደንበኞቻቸውን ወርሀዊ ክፍያ መሰብሰብ የሚየስችላቸው ሲሆን የማህበረሰቡን የዲጂታል ክፍያ ተጠቃሚነት ፍላጎት ለማሳደግም ሚና አለው ተብሏል፡፡

በዚህ መልክ ክፍያን መፈጸም በጥሬ ገንዘብ የሚደረገውን ግብይት ለመቀነስ እና የቢዝነስ መረጃዎችን ፍሰት በቀላሉ ለማወቅ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ገልፀዋል ። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው ተቋሙ
በዋናነት የኢትዮጵያን  የዲጂታልና የሳይበር ሉዓላዊነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ከሌሎች በርካታ ከተሞች ውሀ እና ፍሳሽ አገልግሎቶች ጋርም ስምምነቱን በመፈፀም በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባም ተነግሯል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply