በኢትዮጵያ የግሪን ሀይድሮጂን ለማምረትና ለመጠቀም ምቹ ኹኔታዎች መኖራቸው ተገለጸ

ዕረቡ መስከረም 18 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ የግሪን ሀይድሮጂን ለማምረትና ለመጠቀም ምቹ ኹኔታዎች መኖራቸውን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፤ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው በኮቱዲቯር ዋና ከተማ፤ በአቢጃን እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የግሪን ሀይድሮጂን ፎረም “Africa Green Hydrogen Forum Ahead of COP27” በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በመደርኩ ላይ በሰጡት አስተያየትም፤ ኢትዮጵያ የግሪን ሃይድሮጂን አምራችና ተጠቃሚ ማድረግ ያለው ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች በስፋት ዳስሰው የግሪን ሀይድሮጂን አምራች አገር ለመሆን ቀዳሚ የሚያርጓት ምቹ ኹኔታዎችን አንስተዋል።ሚንስትር ዴኤታው እንደገለጹት፤ የግሪን ሀይድሮጂን ለማምረት ከፍተኛ የሆነ የታዳሽ ሀይል እንደሚያስፈልግና በዚህም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የታዳሽ ሀይል አማራጭ መኖር፤ ከሀይድሮፖወር (45000 ሜጋ ዋት) ከጂኦ-ተርማል (10,000 ሜጋ ዋት)፣ ከንፋስ ኃይል (100 ጌጋ ዋት) እና ከፀሐይ ብርሃን ከፍተኛ ኃይል የማመንጨት አቅም መኖሩን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የምትገኝበት አቀማመጥ ግሪን ሀይድሮጂንን አምርቶ ወደ ገቢያ ለማቅረብ አማራጭ የጎረቤት አገራት ወደቦች መኖራቸው፤ ኢትዮጵያ የምትከተለው ግብርና መር የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ግሪን ሀይድሮጂን ለማምረት ምቹ ኹኔታዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአለማችን አዳጊ የኢነርጂ ፍላጎት ለማርካት የተለያዩ የታዳሽ ሀይል አማራጮች ላይ ጥናትና ምርምር እየተደረገ እንደሚገኝ ይታቃል፤ ከዚህም ውስጥ የግሪን ሀይድሮጂን ማምረት ጥሩ አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡በትናንትናው ዕለት የተጀመረው የአፍሪካ የግሪን ሀይድሮጂን ፎረም “Africa Green Hydrogen Forum Ahead of COP27” ለኹለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ “100 Million tons of green Hydrogen annually by 2030 for climate and Security” በሚል መርህ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ፎረሙ የግሪን ሀይድሮጅን ተቋም ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፤ 12 የአፍሪካ አገራት የሚሳተፋፉበት ሆኖ፤ የግሉ ዘርፍ፣ የልማት አጋሮችና የሲቪል ማህበራትን ማካተቱን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በቅርቡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ግሪን ሀይድሮጂን አሊያንስ አባል አገር እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡

The post በኢትዮጵያ የግሪን ሀይድሮጂን ለማምረትና ለመጠቀም ምቹ ኹኔታዎች መኖራቸው ተገለጸ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply