በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተካታችነትን ለማሻሻል የሚያስችል “አኮፋዳ” የተሰኘ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ፕላትፎርም መጀመሩ ተገለፀ።

ፕላትፎርሙ በሸጋ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ የበለፀገ ሲሆን የሦስት ዓመት “አኮፋዳ” የተሰኘ ፕሮጀክት አካል ነው።

የፕሮጀክቱ አላማ የባለድርሻ አካላትን እውቀት በማዳበር ፤ ለአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች የሚሆኑ አገልግሎቶችን መደገፍ እና የፋይናንስ ተካታችነትን ለማሻሻል ያለመ ነው።

የመረጃ ትንታኔን እና ምልከታን ይዞ የመጣው የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ፕላትፎርም የፋይናንስ ተቋማትን፣የዘርፉ ባለሙያዎችን እና ተጠቃሚዎችን አቅም በማሳደግ የፋይናንስ ዘርፉን ለመደገፍ ያለመ ስለመሆኑም ተገልጿል።

የሸጋ ኢንሳይትስ ማናጀር የሆኑት አቶ ናትናኤል ፀጋው፤ አኮፋዳ በኢትዮጵያ ለሚገኘው የፋይናንስ ዘርፍ አጠቃላይ መረጃ፣ ምልከታና የተለያዩ ግብዓቶችን ያለምንም ክፍያ የሚያቀርብ ፈጠራ የታከለበት ፕላትፎርም መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም አቶ ናትናኤል ፕላትፎርሙ ያለማቋረጥ በሚለዋወጠው የዲጂታል ፋይናንስ ዓለም ፥ ተጠቃሚዎች ያለ ስጋት እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ፕላትፎርሙ በውስጡ ሁሉን አቀፍ መረጃ አቅርቦት የያዘ ሲሆን፤ይህም የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት እና ተያያዥ መረጃዎችን በማቅረብ ተጠቃሚዎች ውሳኔዎች ላይ እንዲደርሱ የሚያደርግ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ጥራት ያላቸው ምልከታዎች ናቸው የተባለ ሲሆን፤ በዘርፉ ለሚገኙ አካላት የአገሪቱን ሁኔታ ያገናዘቡ ምልከታዎችን መስጠት እና የፋይናንስ አገልግሎቱን እንዲረዱ ማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

ሌላኛው የጠቃሚ ግብዓቶች መገኛ ማዕከል ነው። በዚህ ስር ደግሞ ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የዜና ዘገባዎችን ፣ ሪፖርቶችን እና የተለያዩ ግብዓቶችን አጠቃሎ የያዘ ተደራሽ የመረጃ ምንጭ ነው ተብሏል።

እስከዳር ግርማ
ግንቦት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply