በኢዜማም ሆነ በመሪው ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ላይ የተነሱ ጥያቄዎች በጨዋ ደንብ የቀረቡ ቢሆኑም ተገቢ ምላሽ ግን አላገኙም ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ገለፁ፤ ከመድረክ የተሰጡ አጉል ፍረጃና ስድብ…

በኢዜማም ሆነ በመሪው ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ላይ የተነሱ ጥያቄዎች በጨዋ ደንብ የቀረቡ ቢሆኑም ተገቢ ምላሽ ግን አላገኙም ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ገለፁ፤ ከመድረክ የተሰጡ አጉል ፍረጃና ስድብ መድረኩን ጥለን እንድንወጣ አድርጎናል ብለዋል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ግንቦት 8 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ አማራ ሚዲያ ማዕከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ ግንቦት 8 ቀን 2013 በወልድያ ካደረገው ስብሰባ ጋር ተያይዞ በፓርቲውና በዋናነት በመሪው ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ላይ በርካታ ጥያቄዎች እንደተነሱ ለማወቅ ችሏል። አሚማ በስብሰባው ላይ ምን ጥያቄዎች ተነሱ?፣ ከተሳታፊዎች መድረክ ረግጦ የወጣ አለ ወይ?፣ ለምን?፣ በሂደቱስ ከወልድያ አማራ የእንግዳ ተቀባይነትና ዲሞክራሲ መሻት ብሎም ዋጋ የመክፈል አበርክቶቱ የወጣ ነገር ታይቷል ወይ?፣ በፕ/ር ብርሃኑ ላይ የደረሰ ነገር አለን? የሚሉና ሌሎች መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት ተሳታፊዎችን አነጋግሯል። አንደኛው ወጣት ጥያቄዎችን ለማቅረብ እጅ አውጥቶ እድሉን ያላገኘ ሲሆን ሌላኛው ግን እድሉን አግኝቶ ያሉትን ጥያቄዎች ለፕ/ር ብርሃኑ ማቅረቡን ከቆይታችን ለመረዳት ተችሏል። በስብሰባው ከተሳተፉት መካከል ጥያቄያቸውን በጨዋነት ያቀረቡ ቢሆንም ፕ/ር ብርሃኑ በጥያቄዎቹ ስሜታዊ ሆነው ወደ አጉል ፍረጃ እና ስድብ በመግባታቸው በርካታ ተሳታፊዎች ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውን፣ እሳቸውም በሰላም እንዲወጡ መጠየቃቸውንና ያለኮሽታ ወደ ደሴ መሸኘታቸውን አሚማ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች ገልፀዋል። ከወልድያ አማራ ጨዋ የእንግዳ አቀባበልና ከዲሞክራሲያዊ አካሄድ ያፈነገጠ አቀራረብ አስመስለውና ፈርጀው የሚገልፁ የአንዳንድ አካላት አገላለጽ ትክክል አለመሆኑንም ተናግረዋል። ከተነሱት በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንደኛው ፕ/ር ብርሃኑ የተናገሩት በተንቀሳቃሽ ምስል የቀረበው ሀገር ገንቢውን አማራን በቤንሻንጉል ጉምዝ እንደ “መጤ” አድርገው መግለጻቸው ትክክል አለመሆኑን የሚያሳይ ይዘት ያለው ሲሆን ጥያቄ አቅራቢው በመጀመሪያ የእሳቸውን ንግግር በሞባይሉ በመክፈት በጨበጠው ማይክ ለተሳታፊዎች እንዲሰማ ማድረጉ ፕ/ሩን ክፉኛ ከረበሿቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ እንደነበር ተገልጧል። ፕ/ር ብርሃኑ ከሙስና ጋር አያይዘው ቤተ ክርስቲያንን እንደ ማሳያ መጥቀሳቸውና የልዩ ኃይል አደረጃጀት ኢ ህገ መንግስታዊ ነው፤ ይፍረስ ከማለታቸው በፊት በተለይም ትሕነግ ጁንታውን ከመከላከያ ጋር ሆኖ ለተፋለመውና ሀገር ላስከበረው ለአማራና ለአፋር ልዩ እውቅና አለመስጠታቸው በተሳታፊዎች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ እንደነበር ተገልጧል። ከተጠየቁት ጥያቄዎች መካከልም:_ አማራ የለም ካላችሁ ለድምፅ ሲሆን እንዴት አገኛችሁት፣ አማራ የእርስት ባለቤት እንጅ መጤ እንዴት ይባላል?፣በአማራ ላይ የሚፈፀምን የዘር ፍጅት ግጭት ለምን ይባላል? የሚሉት ይገኙበታል። በመድረኩ ከአሁን ቀደም ለአርበኞች የተሰበሰበው 30 ሚሊዮን ዶላር ለታጋዮች እንዲመለስም ተጠይቋል ብለዋል_ተሳታፊዎቹ። በተጨማሪም 1997 የኢትዮጵያን ድምፅ አሳልፎ ለኢሕዴግ የሸጠው ማን ነው? አቶ ልደቱ አያሌዉ ወይስ አንተ?፣ ከልደቱ አያሌው ጋር የፊት ለፊት ውይይትን ለምን አልተቀበልክም?፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት ትጥቅ ፈቶ ሲገባ ኦነግ ከእነ ትጥቁ እንዲገባ የአንተ እጅ አለበት? የሚሉ ጥያቄዎችም ለፕ/ር ብርሃኑ ከተሳታፊዎች ተነቶላቸው እንደነበር ተነግሯል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply