በኤርትራ ጦርም ሆነ በሀገር ውስጥ የፀጥታ ሀይሎች በትግራይ ክልል ተፈፅመዋል የተባሉት የመብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል ይጠራል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከባለፈው ሳምንት የአምነስቲ ኢንተርናሽል ሪፖርት በፊትና በኋላ በትግራይ ክልል ስላለው ድህረ ጦርነት የመብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል ይጣራ የሚለው ጥያቄ ለኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡

ከትናንት በስቲያ እንኳን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት የኤርትራ ጦርና የአማራ ልዩ ሀይል ከትግራይ ክልል በአፋጣኝ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ይህንኑ አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት በሳምንታዊው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ መንግስት ግብዣ ተደርጎለት፣ እውቅና አግኝቶ እንዳልተሳተፈ አረጋግጠዋል፡፡

ይሁንና ከሁለቱ ሀገራት የድንበር ሁኔታና ከህወሓት በኩል ሲሰነዘሩ ከነበሩ ሚሳኤልን ጭምር ካካተቱ ጥቃቶች አኳያ ወታደሮች ሲገቡና ሲወጡ ሊስተዋል ይችላል ብለዋል፡፡የአማራ ክልል ልዩ ሀይልን በተመለከተ ግን የሀገር ውስጥ የፀጥታ ሀይል እንደመሆኑ መጠን ጥያቄው ተቀባይነት የለውም ሲሉ ውድቅ አድርገውታል፡፡

ከመብት ጥሰቶቹ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግስት አቋም በሂደት ይጣራ የሚል እንደሆነ አምባሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡አንቶኒ በሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በነበራቸው ቆይታ በትግራይ ክልል ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሠጪ ተቋማት ገብተው እንዲንቀሳቀሱ ኢትዮጵያ መፍቀዷን ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡

ቀን 25/06/2013

አሐዱ ራዲዮ 94.3

Source: Link to the Post

Leave a Reply