በእስር ላይ በሚገኙት የኢሰመጉ ሰራተኞች ላይ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 3 ቀን 2015 ዓ/ም አ…

በእስር ላይ በሚገኙት የኢሰመጉ ሰራተኞች ላይ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 3 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ላለፉት ስድስት ቀናት በእስር ላይ በሚገኙት አራት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ሰራተኞች ላይ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጓል። የኢሰመጉ ሰራተኞች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ለመመልከት ለነገ ሐሙስ ጥር 4፤ 2015 በፍርድ ቤት ቀጠሮ ተሰጥቷል። የኢሰመጉ ሶስት የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች እና አንድ አሽከርካሪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች እየተካሄደ የነበረ “የቤት የማፍረስ ዘመቻን ለማጣራት ተሰማርተው” በነበረበት ወቅት እንደሆነ ጉባኤው አስታውቆ ነበር። አራቱ የኢሰመጉ ሰራተኞች ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ታህሳስ 27 በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ አስተዳደር ገላን ጉዳን ክፍለ ከተማ እንደሆነ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ገልጿል። አራቱ የድርጅቱ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር በዋሉ ማግስት፤ በኦሮሚያ ክልል የሰበታ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው አምስት የምርመራ ቀናት ተፈቅዶባቸው ነበር። በእለተ ረቡዕ ጥር 3፤ 2015 ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ በቀረቡት የኢሰመጉ ሰራተኞች ላይ፤ መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናትን መጠየቁን ጠበቃቸው አቶ አዲሱ አሸናፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። መርማሪ ፖሊስ በዛሬው ችሎት፤ ተጠርጣሪዎቹ “ከመስሪያ ቤታቸው ደብዳቤ ሳይዙ በቦታው ላይ ለምርመራ መሰማራታቸውን” ለፍርድ ቤት ማስረዳቱን ጠበቃው ገልጸዋል። ተጠርጣሪዎቹ “ከፖሊስ ፍቃድ ሳያገኙ የፖሊስ ታፔላን ፎቶ አንስተዋል” የሚል ውንጀላ እንደቀረበባቸውም አቶ አዲሱ አክለዋል። የኢሰመጉ ሰራተኞች “በብሔር እና ብሔር መካከል ጠብን በሚቀሰቅስ መልኩ፤ ‘ቤቶች እየፈረሱ ያሉት ለአንድ ብሔር የወገነ በሚመስል መንገድ ነው’ እያሉ ነበር” ሲል መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤት መናገሩን ጠቅሰዋል ሲል ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply