
በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የሚመሰክሩ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ይሰሙ መባሉ ውድቅ ተደረገ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ «ምንም አይነት ከመጋረጃ ጀርባም ሆነ በዝግ የሚደረግ ምስክርነት አሰጣጥ አይኖርም» ያሉት የእነ እስክንድር ነጋ ጠበቃ አቶ ቤተ ማርያም ዓለማየሁ ናቸው። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ፀረ-ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዩች ችሎት አቃቤ ሕግ በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የሚመሰክሩ ምስክሮቼ ከመጋረጃ ጀርባ ይሰሙልኝ በሚል ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አደረገ። ባለፈው የችሎቱ ውሎ አቃቤ ሕግ የምስክሮች ጥበቃ አዋጅን መሠረት በማድረግ ለምስክሮቼ ደህነት ሲባል ከመጋረጃ ጀርባ ኾነው ይመስክሩ በሚል ተከራክሮ ነበር። ጠበቆች በበኩላቸው ይህን ተቃውመዋል። ከነ እስክንድር ጠበቆች አንዱ የኾኑት አቶ ቤተ ማርያም ዓለማየሁ፦«ችሎቱ ዛሬ የደረሰበት ድምዳሜ ምስክሮች በአካል ቀርበው መመስከር ስላለባቸው ስለዚህ ምንም አይነት ከመጋረጃ ጀርባም ኾነ በዝግ የሚደረግ ምስክርነት አሰጣጥ አይኖርም በሚል የአቃቤ ሕግን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ቀጣይ የአቃቤ ሕግን የክስ መሻሻል ለመጠበቅ ለታኅሣስ 13 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ጠዋት ሁለት ሰዓት ተኩል ተቀጥሯል» ብለዋል። የእነ እስክንድር ነጋ ጠበቆች በመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያቸው ዘርዘር ያሉ ጉዳዮችን ቢያቀርቡም ችሎቱ በኹለት ጉዳዮች ብቻ ትኩረት ሰጥቷል። አንደኛው ተከሳሾች መገናኛ ብዙኃን በመጠቀም ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ ቅስቀሳ አድርገዋል ለሚለው በየትኛው የሚለው እንዲጠቀስ፤ ኹለተኛም አራተኛዋ ተከሳሽ ወይዘሮ አስካለ ለብሔር ግጭቱ ሰዎች ትመለምል ነበር ለሚለው የሰዎቹ ማንነት ተዘርዝሮ ክሱ እንዲቀርብ ችሎቱ መጠየቁን ከአዲስ አበባ ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር የላከልን ዘገባ ያስረዳል ሲል DW ዘግቧል።
Source: Link to the Post