በእነ እስክንድር የክስ መዝገብ ዐቃቤ ሕግ “12ቱ ምስክሮች እንደታለፉ ይመዝገብልን ” አለ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 7 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የፌዴ…

በእነ እስክንድር የክስ መዝገብ ዐቃቤ ሕግ “12ቱ ምስክሮች እንደታለፉ ይመዝገብልን ” አለ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 7 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በእነ እስክንድር ነጋ የክስ መዝገብ ዐቃቤ ሕግ አስቀድሞ ያስመዘገባቸው እና ቀሪ ምስክሮች እማኝነታቸውን እንዲሰጡ ፤ እንዲሁም ማንነታቸው ያልታወቁት 12ቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ማንነታቸው ተገልጾ እንዲቀርቡ በተሰጠው ትዕዛዝ ኅዳር 6 ቀን 2014 ዓ.ም ችሎቱ የተሰየመ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ አስቀድሞ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ምስክሮች አልተደመጡም። ዐቃቢ ሕግ በዋለው ችሎት እንደገለጸው “8ኛ እና 9ኛ ቀሪ ምስክሮች በፍ/ቤቱ መጥሪያ እንዲቀርቡ ፣ ለፌደራል ፖሊስ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት ያመለከትን ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ ፖሊስ አልደረሰኝም ” በማለቱ ምስክሮችን ማቅረብ አልቻልኩም ብሏል ። የተቀረው 1ኛው ምስክር ” በኮሮና በሽታ ምክንያት ታመው የነበሩ ሲሆን ፣ አሁንም ስላልተሻለው ኅዳር 7 ቀን 2014 ዓ.ም መቅረብ እንደሚችል ” ዐቃቤ ሕግ ለፍ/ቤት ገልጿል። ማንነታቸው ያልታወቁቱ 12ቱ ምስክሮችን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ስም ዝርዝር እና ማንነታቸው በግልጽ እንዲቀርብ እና እንዲያስመሰክር ለዐቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም ፤ “12ቱ ምስክሮች እንደታለፉ ይመዝገብልን። ቀሪ ምስክሮችን ማሰማታችንን እንቀጥላለን ፤ ሂደቱን ጠብቀን ይግባኝ እንጠይቃለን ” በማለት ምላሽ ሰጥቷል። በዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረበውን ምላሽ አስመልክቶ የተከሳሾች ጠበቆች በሰጡት የተቃውሞ መልስ ፦ 12ቱ ምስክሮችን በተመለከተ ፍ/ቤቱ ተገቢውን ትዕዛዝ ሰጥቷል፤ ሆኖም ግን በዛሬው ቀጠሮ ስም ዝርዝር እና ማንነታቸው በግልጽ እንዲቀርቡ የተሰጠው ትዕዛዝ ዐቃቤ ባለማክበሩ በፍርድ ቤት የተሰጠው መብት እንዲታለፍ፣ በኮሮና ታሟል የተባሉት ምስክር ስለ መታመማቸው ፍርድ ቤቱ የህክምና ማስረጃ እንዲያቀርብ ለዐቃቤ ሕግ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም ማስረጃ መቅረብ አልቻለም። በዛሬው ዕለት ይጠበቅ የነበረው ምስክርነታቸው ማሰማት አልቻሉም ፤ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ባለማክበር በዘፈቀደ ምስክሬን እንዳሰማ ይደረግልኝ ማለት አግባብ አይደለም ። የተቀሩት ሁለትን ምስክሮች በተመለከተ፤ ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩን በአግባቡ ተከታትሎ ፣ የፍርድ ቤት የመጥሪያ ትዕዛዝ እንዲደርስ በማድረግ ምስክሮችን በማቅረብ የፍ/ቤት ትዕዛዝ ማስፈጸም ሲገባው፤ ሆን ብሎ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ችሎቱን ለማጓተት እና ለማዘግየት ፈልጎ ስለሆነ በዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረበው ምክንያት ውድቅ መደረግ አለበት ። ከላይ ባቀረብናቸው ምክንያቶች ፤ ዐቃቤ ሕግ በቂ እና አሳማኝ ምክንያቶች ባለማቅረቡ ፣ከዚህ ቀደም አቅርቦ ባሰማቸው ምስክሮች ብቻ ተገቢውን ትዕዛዝ ይስጠን ፤ በማለት ለዐቃቤ ሕግ ምላሽ ሰጥተዋል ። የግራና ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት ፤በኮሮና በሽታ ምክንያት ታመው የነበሩ ምስክር ማክሰኞ ኅዳር 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጠዋት ቀርበው እንዲመሰክሩ ። ሁለቱ የዐቃቤ ሕግ 8ኛ እና 9ኛ ቀሪ ምስክሮች የፍርድ ቤት መጥሪያ እንዲደርሳቸው እና ሐሙስ ኅዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም ቀርበው እንዲመሰክሩ፤ እንዲሁም ማንነታቸው ያልታወቁት 12ቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በተመለከተ በነገው ዕለት ውሳኔ ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል ። ከችሎት ዘገባ ጋር በተያያዘ ፤ የምኒልክ ቴሌቭዥን ጋዜጠኛ አዲሱ ደረበ በእነ እስክንድር የክስ መዝገብ አዘጋገብ ጋር በተያያዘ ፤ ዐቃቤ ሕግ በመሰረተበት ክስ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርቧል። በቀረበበት ክስ ላይ መልስ ይዞ እንዲቀርብ ለረቡዕ ኅዳር 8 ቀን 2014 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል። 4ኛ ተከሳሽ ወ/ሪት አስካለ ደምሌ ከቤተሰብ ጋር የስልክ ግንኙነትን እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡትን አቤቱታ አስመልክቶ ብይን ለመስጠት ለነገ ጠዋት ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ዜናው የባልደራስ ሚዲያ ክፍል ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply