“በእኛ የደረሰው ግፍ በጠላትም አይድረስ” ከሕወሓት አፈና የተረፈ የሰሜን እዝ የ23ኛ ክፍለ ጦር አባል_ለቤተሰቦቹ ደህንነት ሲባል ስሙ ያልተጠቀሰ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ… ህዳ…

“በእኛ የደረሰው ግፍ በጠላትም አይድረስ” ከሕወሓት አፈና የተረፈ የሰሜን እዝ የ23ኛ ክፍለ ጦር አባል_ለቤተሰቦቹ ደህንነት ሲባል ስሙ ያልተጠቀሰ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ… ህዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ከ21 አመት በላይ ካገለገልኩበት ከተማርኩበት፣ ትዳር፣ ቤት ከመሰረትኩበት፤ ልጅ ከወለድኩበት ትግራይ ውስጥ ከ27 ቀናት በላይ ከጓደኞቼ ጋር ታፍነን ቆይተናል ይለናል የሰራዊቱ አባል፡፡ ጉዳዩ የተፈጸመው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ማክሰኞ ምሽት 4:00 ነበር፤ ነገሮች ቀድመው ውስጥ ለውስጥ አልቀዋል፤ ከሰራዊቱ የተደበቁ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ጊዜና ስዓት የእዙ ሠራዊት ባሉባቸው አካባቢዎች (ዳንሻ፣ ኩያ ላጭ (መቀሌ)) ላይ ባልጠበቅነው ሁኔታ ከጥበቃዎቻችን ጋር የተኩስ ልውውጥ ተደረገ፡፡ እኛም ስልጠና ልምምድ ላይ ናቸው ብለን በቤታችን ውስጥ ቆየን፡፡ ከትግራይ ፈጥኖ ደራሽ (ልዩ ሃይል) ጋር አብረን አንበጣ አባርረናል፤ እህል አጭደናል፤ የደሃ ቤቶችን ሰርተናል፤ በደስታውም ሆነ በሃዘን ክፉ በጎ አሳልፈናል፤ በእኛ ላይ ክህደት ይፈጽማሉ ብለን አስበን አናውቅም፡፡ ባልታሰበ ሁኔታ አፈና ተደረገብን፤ የአፈናው ሰለባ የሆኑትም ቢሮ ላይ ያሉት የስታፍ አባለት፣ የአየር ሃይልና ልዩ ልዩ ወታደራዊ ሙያ የሚሰለጥኑ ተማሪዎችና ውጊያ ላይ ቆይተው ጥይት ጨርሰው የተማረኩት ናቸው፡፡ በኤርትራ ድንበር ምሽግ ላይ የነበሩት ብዙም ጥቃት አልደረሰባቸውም፤ ጉዳዮ ከተፈጠረ በኀላ የእዝ ሰንሰለቱ ስለተቆራረጠ መገናኘትና መልስ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በአጠቃላይ ከ6-10 ሽህ የሰራዊቱ አባላት ታፍነን ቆይተናል፤ በየጊዜው ወደተለያዩ ቦታዎች ይወስዱናል፡፡ የታፈነውን ሰራዊት (ከፍተኛ አመራሮች፣ ሴቶች፣ ልዩ ሙያ ያላቸው(የፓይለት ሰልጣኞች፣ ኢንጅነሮች፣ መካኒኮች የመድፍና ሚሳኤል ጥገና ባለሙያዎች) እና ባማ (ከአስር አለቃ እስከ ባሻ)) በሚል በ4 ከፈሉን፤ ከአስር አለቃ እስከ ባሻ ማዕረግ ያለንን ተንቤን ውስጥ አግቤ ወሰዱን፡፡ ከጥቅምት 25 -29/2013 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ 4 ቀናት ያለምግብ ቆይተናል፡፡ ተንቤን ላይ ሊረሽኑን ነበር፤ የአካባቢው ህዝብ እንዳትገድሏቸው ብሎ ጮኸ፡፡ ከዚያ ፎርም አስሞሉን፤ 3 አማራጮችን አቀረቡልን፤ 1ኛ ወደ ቤተሰብ መሄድ የሚፈልግ፤ 2ኛ በዚሁ በሰሜን እዝ ሆኖ ከእኛ ጎን የሚሰለፍ፤ 3ኛ ትግራይ ክልል ውስጥ እንደማንኛውም ዜጋ መኖር የሚፈልግ፤ በሚል ተሰጠን ከ3 ልጆች ውጭ ሁሉም ወደ ቤተሰባችን የሚለውን መረጥን፤ ፎርሙ ሙያ፣ ብሄር፣ ማዕረግ ይጠይቅ ነበር፤ ከዚያም የሞላነውን መረጃ ተመልክተው ሴቶችን፣ ከፍተኛ አመራሮችን፣ የፓይለት ተማሪዎችን፣ ኢንጅነሮችንና መካኒኮችን ለይተው አስቀሯቸው፡፡ እኛን በመሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ መኪና ጭነው ተከዜ የሃይል ማመንጫ ግድቡ ኣካባቢ ጣሉን፤ ከዚህ በኀላ ከፈለጋችሁት ድረሱ አሉን፡፡ እኛም ባገኘነው መንገድ ከ3 ቀናት በላይ ተጓጉዘን በየዳ ወረዳ ልዋሬ ቀበሌ ደረስን፤ በመንገድ ላይ በድካም እና በርሃብ ከ20 በላይ የሰራዊቱ አባላት ሞተዋል፤ የለዋሬ ህዝብ በጉልበቱ ተሸክሞ፣ በበቅሎ ጭኖ በየዳ ድልይብዛ አደረሰን፤ በየዳዎችም በሬ አርደው፣ ህክምና ሰጥተው ተንከባክበው ለዚህ አደረሱን፤ ደባርቅ ላይም የተደረገልን እንክብካቤና አቀባበል የደረሰብንን ግፍና በደል የሚያስረሳ ነው፤ ከዚህ ስንደርስ ውሳኔያችን ትክክል ነበር አልን፡፡ ትግራይ ላይ የደረሰብን በደል፦ ሚሊተሪያችን አስወልቀው በፓንት ሰደዱን፤ ሽሬ ከተማ ላይ ከህብረተሰቡ በርበሬ ተቀብለው ከፊታችን ላይ ደፉብን፤ የሰራዊቱ ባለቤቶችና ቤተሰቦች የት እንዳሉ አይታወቅም፤ መንግሥት አሁን የመቀሌ ከተማን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል፡፡ ታፍነው ለቀሩት አባላት በፍጥነት ሊደረስላቸው ይገባል፡፡ ጨካኞች አረመኔዎች ናቸው፤ መረጃ ካላዎጡና ከእነሱ ጎን ተሰልፈው ካልተዋጉ ሊገድሏቸው ይችላሉ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ከ1100 በላይ ከጭፍጨፋ የተረፉት የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ደባርቅ ደርሰዋል። ህዝቡ ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል። ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ አገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው። ከጭፍጨፋ የተረፉት የመከላከያ ሰራዊት አባላት በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ግቢ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል። የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት በተደረገላቸው የክብር አቀባበል ደስታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ታይተዋል።ሰሜን ጎንደር ኮሚዩኒኬሽን!

Source: Link to the Post

Leave a Reply