
“በኦህዴድ/ኦነግ ብልጽግና መንግስት ፍላጎት እና ግፊት ሕዉሃትን ከሽብርተኝነት መዝገብ በመፋቅ የተደረሰበት የፖለቲካ ዉሳኔ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር አዲስ ፀረ-ኢትዮጵያ ቅኝት ያለዉ የሃይል አሰላለፍ የሚፈጥር ነዉ።” የባልደራስ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ … መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ሕወሓትን ከሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ የፋቀውን የመንግሥት እርምጃ በተመለከተ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ:_ ሕወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ትግራይ ውስጥ ሰፍሮ በነበረው በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዋነኛ ክፍል በነበረዉ በሰሜን እዝ ላይ በክህደት ላይ የተመሰረተ ድንገተኛ የጥቃት እርምጃ በመውሰድ:_ 1) በርካታ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በአንድ ሌሊት በተኙበት በመረሸን፣ 2) በወልቃይት ማይካድራ ከተማ ውስጥ ይኖር የነበረውን ሰላማዊ ህዝብ በአሰቃቂ ሁኔታ በአንድ ጀምበር በመጨፍጨፍ፣ 3) ከአማራና ከአፋር ህዝብ ጋር ጦርነት ከገጠመበት ጊዜ ጀምሮ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዝብ ክንዱን በማስተባበር እና ከፌደራል መንግስቱ ጎን በመቆም የሕወሓትን እኩይ ሀገር የማፍረስ አላማ እንዲያከሽፍ ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል። ሕወሓት በ2010 ዓ.ም በህዝባዊ ዓመፅ እስከተወገደበት ጊዜ ድረስ የነገድ እና የጎሳ ፖለቲካን ሕገመንግሥታዊ መሠረት እንዲኖረው በማድረግ፣ ላለፉት 30 ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝብ በጎሳና በነገድ እንዲከፋፈል በማድረግ ረገድ በሀገረ ኢትዮጵያ አንድነት ላይ ታሪክ ሁልጊዜም በእኩይነቱ የሚያስታውሰው ሃጢያት ፈጽሟል። አንድነቱና ህብረቱ እንዲላላ በማድረግ የኢትዮጵያን ህዝብ አሁን ወደ ደረሰበት ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ቀውስ እንዲያመራ በር የከፈተ፣ በጽንፈኛ የነገድ ፖለቲካ የተመረዘ ፓርቲ ነው። ሕወሓት ለሶስት አስርተ ዓመታት የዘለቀ ፀረ-ኢትዮጵያዊ አቋም ያደረሰውን ሀገራዊ ቀውስ በሚገባ የሚረዳው ባልደራስ፣ የሰሜን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ ሕወሓትን በተመለከተ ይዞት የነበረው ጽኑ አቋም ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ ነበር። እነሱም፦ 1ኛ. ሕወሓት በጫረው ጦርነት የሚገፋበት ከሆነ፣ ሰሜን እና ደቡብ ወሎን እንዲሁም የአፋር ሰሜን-ምዕራብ አካባቢዎችን በመውረር አዲስ አበባን ለመያዝ እና የጅቡቲ የባቡር ሃዲድ መስመርን ለመቁረጥ በጦርነቱ እየገፋ መጥቶ ብዙ ጥፋት ካደረሰ በኋላ፣ ስራዊቱን ለማገዝ በዘመቻ ከተመመው ከአማራ እና አፋር ልዩ ሃይል፣ ከአማራ ፋኖ እና ሚሊሽያ ጋር በመሆን ጥምር ጦሩ ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት እንደተሽጋገረ፣ የህዉሃት ወታደራዊ ሃይል ሙሉ በሙሉ ተንኮታክቶ እስኪፈርስ ድረስ ጦርነቱ ሳይቋረጥ ህዉሃት ሙሉ በሙሉ ተሸንፎ ትጥቁን እስከሚፈታበት ጊዜ ድረስ እንዲቀጥል። 2ኛ. ህወሓት ከፀረ-ኢትዮጵያ አቋሙ እስከ ወዲያኛው ድረስ ሊላቀቅ የሚችል ባለመሆኑ ከሽብርተኝነት ሊስት ሊፋቅ ስለማይችል ሌሎች የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች በትግራይ ውስጥ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የሚደረግበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚሉ ናቸው፡፡ ይሁንና እነዚህ ሁኔታዎች ሳይሟሉ የህወሓት ጦር ተሽነፎ ወደ ትግራይ ካፈገፈገ በኋላ፣ ጦርነቱ ተገፍቶ ትግራይ ድረስ ዘልቆ በመግባት ህወሓትን ትጥቅ ማስፈታት ሲቻል፣ የርእዮት ዓለምና እና የፖለቲካ አላማ ተመሳሳይነት ባለው የኦህዴድ/ኦነግ ብልጽግና መንግስት ትእዛዝ ጦረነቱ ሳይቋጭ እንዲቆም ተደረገ። በእብሪት የተወጠረውና በተለይ የአሜሪካንንና የምእራባውያን መንግስታትን አይዞህ ባይነት በማግኘቱ የልብ ልብ ተሰምቶት የነበረዉ ህወሓት በጥምር ጦሩ ተደቁሶ ወደ ትግራይ ከማፈግፈጉ በፊት ወደ አማራና አፋር ክልል ዘልቆ ገብቶ በነበረበት ጊዜ በርካታ የጦር ወንጀሎችን በንፁሃን የአማራና የአፋር ህዝብ ላይ መፈጸሙ ይታወቃል። ሕወሓት ከጥንስሱ ከሚታወቅበት አንደኛው ጠባዩ የነገድ ጽንፈኝነቱ እና ሽብርተኝነቱ ነው። ሕወሓት በወልቃይት ማይካድራ ከተማ ነዋሪዎች ፣ በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን እና ደቡብ ወሎ እንዲሁም በአፋር ህዝብ ላይ የፈፀመውን ተከታታይ የሽብር ወንጀል ተከትሎ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከተባባሪው ኦነግ ሸኔ ጋር በሽብርተኝነት አብሮ እንዲፈረጅና የሽብር እንቅስቃሴው እንዲገታ ባልደራስን ጨምሮ ሰላም ወዳድ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ አበክሮ መንግሥትንና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ሲጠይቁ ቆይተዋል። በዚሁም መሠረት ሕወሓት በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 28/2013 ዓ.ም ሽብርተኛ ተደርጎ ለመፈረጅ በቃ። የምክር ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ሕወሓትን ከማንኛውም የፓርቲ እንቅስቃሴ በማገድ የፓርቲውን ህልውና እንዲያከትም አደረገ። በሶስተኛዉ ዙር ጦርነትም ጥምር ጦሩ እንደ ሁለተኛዉ ዙር ጦርነት ሕወሃት ሳይቀናው ቀርቶ በርካታ የትግራይ ከተሞች በጥምር ጦሩ ተይዘዉ መቀሌም በመከላከያ ጦር ተከቦ የሕዉሃት መሪዎች ከሃገር ለመውጣት ወይ እጅ ለመስጠት በተቃረቡበት ጊዜ፣ ለሁለተኛ ጊዜ የኦህዴድ/ ኦነግ ብልጽግና መንግስት ቋሚ የርእዮተአለም አንድነት እና የአማራ ጥላቻ ላቆራኘው ለህወሓት በመራራት ከሁለገብ ሽንፈት ታደገዉ። በኦህዴድ/ኦነግ ብልፅግና መንግሥት በኩል ይኼ መደረጉ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ጦርነቱ ያስከተለው የሀገር ውድመት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ሆኖ ባለበት በአሁኑ ጊዜ በተቻኮለ ሁኔታ መደረጉ የሚገርም ነው፡፡ ስንትና ስንት ወጣት በግፍ አስጨርሶ ስንትና ስንት ወላጅ ደም እምባ አስለቅሶ ንብረትና ልማት አውድሞ ደምስሶ አሸባሪ ተብሎ በወንጀል ተከሶ እንዴት አጋር ሆነ ዛሬ ተመልሶ? የመከላከያን ዋንኛውን ክፍል ሰሜን እዝን ደምስሶ ሚሳኤል ሮኬት ወደ ህዝብ ተኩሶ አሸባሪ ተብሎ በወንጀል ተከሶ እንዴት አጋር ሆነ ዛሬ ተመልሶ፤ በችኮላ ደርሶ? ምዕራባውያን አጋሮቹ በተለየም አሜሪካ ሕወሃት በጦርነት ያልተሳካለት እና አቅም ያጣ መሆኑን ተገንዝበው በሰላም ድርድር ሽፋን እራሱን እንዲያድን ስለመከሩት፣ በኦህዴድ ብልጽግናም ላይ ከባድ የኢኮኖሚ ጫና በማድረግ ስላንበረከኩት፣ እራሱም ሕወሃት ቀኑ እየጨለመበት መሆኑን ሲረዳ ፣ የጮሌ ፖለቲካውን በመጫወት ሰላም ፈላጊ በመምሰል፣ የሥልጣን ፉክክር ካልሆነ በቀር ምንም የፖለቲካ ዓላማ ልዩነት ከሌለው የኦሮሙማ መራሹ የኦህዴድ/ኦነግ ብልጽግና መንግሥት ጋር በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ “ለድርድር” እንዲቀመጡ እና “ስምምነት” እንዲፈራረሙ ተደረገ። የፕሮቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 6 (F) መሠረት ትህነግ (የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር) በ30 ቀናት ውስጥ የከባድና የቀላል መሣሪያ ትጥቅ እንዲፈታ እና በስምምነቱ አንቀጽ 3 (5) መሰረት ተጠቅሶ እያለ፣ የሀገር የመከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ገብቶ ፀጥታ የማስከበሩን ሥራ በተገቢው ሁኔታ እንዲረከብ ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ ቡድኑ ትጥቅ ሳይፈታ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሙሉ ለሙሉ ከትግራይ ለቆ በወጣበት ሁኔታ፣ አንድም አይነት ሀገራዊ ምክክር ሳይደረግበት፣ የኦህዴድ/ኦነግ ብልጽግና መንግሰት በተቻኮለ ሁኔታ ሕወሃት ከሽብርተኝነት መዝገብ እንዲፋቅ አደረገ። ከሽብርተኝነት ሊስት እንዲፋቅ የተደረገበትም የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ስብሰባ እራሱን የቻለ ትዕይንት ነበር። በስብሰባው ወቅት አብዛኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባልተገኙበት ከተገኙትም መሃል ከ60 በላይ ተወካዮች ተቃውሟቸውን እያሰሙ የነበሩበት፣ ጥቂቶች ደግሞ ድምፀ-ተአቅቦ ያደረጉበት ሁኔታ አብዛኛው የምክር ቤት አባላት ሕወሃትን ከሽብርተኝነት መዝገብ መፋቅ “የተስማሙበት” አካሄድ የተለመደዉ ኢህአዲግአዊ ድርጅታዊ ጥርነፋ በፓርላማው ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ በመዋሉ ምክንያት መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ ሕወሃትን ዳግም የአራት ኪሎ ስልጣን ተጋሪ እንዲሆን የሚያደርግ ውሳኔ ለቀጣይ ሌላ አራተኛ ዙር ግጭትና ጦርነት ህዝብና ሀገርን ሊያጋልጥ የሚችል ፀረ-ሀገራዊ ውሳኔ በመሆኑ፣ ባልደራስ ውሳኔውን በፅኑ ይቃወማል፡፡ በተጨማሪም አግባብነት በሌለው ውሳኔ በሀገራችንና በህዝባችን ላይ ለሚደርሰው አደጋና ጥፋት የኦሕዴድ/ኦነግ የኦሮሙማው የብልፅግና መንግሥት ሙሉ ኃላፊነት የሚወስድ መሆኑን በአንክሮ ያስገነዝባል፡፡ በአፋርና በአማራ ክልል ነዋሪ ህዝብ ላይ ቡድኑ በፈፀማቸው የጦር ወንጀሎች ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦችንና ግለሰቦችን ሳይካሱና ለጠፋው ሀብትና ንብረት ካሳ ሳይከፈል፣ ክፉኛ በተቋሰለዉ ህዝብ መካከል እርቅና ስምምነት ሳይደረስ፣ ጉዳዩ ሀገራዊ እንደመሆኑ በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲወያዩበት ሳይደረግ፣ በገዥ ፓርቲዉ ብቸኛ ዉሳኔ የአንድን ወንጀለኛ ቡድን የማበረታታት እና የመደገፍ ሥራ መስራት ተገቢ እና ቅቡልነት የሌለው ተግባር መሆኑን ባልደራስ በፅኑ ያምናል። በመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራና በአፋር ህዝብ ልዩ ኃይል፣ በአማራ ፋኖ እና ሚሊሻ በአጠቃላይ በጥምር ጦሩ ከፍተኛ መሰዋዕትነት የተገኘው ድል በኦሮሙማዉ የብልጽግና መንግሥት የተሳሳተ ውሳኔና ትዕዛዝ እየተቀለበሰና ለሌላ አራተኛ ዙር እልቂትና ውድመት ህዝብ ተጋላጭ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑ ግንዛቤ ሊጨበጥበት ይገባል። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ባልደራስ ለጀግኖች የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራና አፋር ህዝብ ልዩ ኃይል፣ ለአማራ ፋኖ እና ሚሊሻ የሀገራችን ኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር ለከፈሉት የህይወትና አካል መስዋእትነት ላቅ ያለ አድናቆትና አክብሮት ያለዉ መሆኑን በድጋሚ እየገለጸ፣ ለሀገር አንድነት እና ሉአላዊነት፣ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት የሚደረግ መስዋእትነት ሁልጊዜም ታሪክ የማይረሳው፣ በታሪክ የክብር መዝገብ ላይ ሰፍሮ ሲዘከር የሚኖር መሆኑ ሊታወቃል ይገባል፡፡ መጋቢት 13/2015 ዓ.ም በኦህዴድ/ኦነግ ብልጽግና መንግስት ፍላጎት እና ግፊት ሕዉሃትን ከሽብርተኝነት መዝገብ በመፋቅ የተደረሰበት የፖለቲካ ዉሳኔ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር አዲስ ፀረ-ኢትዮጵያ ቅኝት ያለዉ የሃይል አሰላለፍ የሚፈጥር ነዉ። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት፣ሰላም እና ደህንነት ያሳስበናል፣ ሰፍኖ የሚገኘዉ አምባገነናዊ የነገድ ፖለቲካ በዲሞክራሲያዊ ስርአት ሊተካ ይገባዋል በሚል የትግል ሰንደቅ ስር የተሰለፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ የሲቪል ማህበራት እና ህዝባዊ ድርጅቶች ጸረ ህወሃት ብቻ ሳይሆን ጸረ ኦህዴድ/ኦነግ ብልፅግና ጭምር የሆነ ሰፊ ሃገራዊ የፖለቲካ ግንባር ሊፈጠር ስለሚቻልበት ሁኔታ ምክክር ሊያደርጉበት ይገባል።
Source: Link to the Post