በኦሮሚያ ከልል በጉጂ ዞኖች ውስጥ የሚፈፀሙ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን አስመልክቶ የሰላም፣ የፍትሕና ተጠያቂነት ጥሪ ቀረበ። “ሴንተር ፎር አድቫንሰመንት ኦፍ ራይትስ ኤንድ ዴምክራሲ”…

በኦሮሚያ ከልል በጉጂ ዞኖች ውስጥ የሚፈፀሙ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን አስመልክቶ የሰላም፣ የፍትሕና ተጠያቂነት ጥሪ ቀረበ።

“ሴንተር ፎር አድቫንሰመንት ኦፍ ራይትስ ኤንድ ዴምክራሲ” (የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ካርድ) የተሰኘው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በኦሮሚያ ከልል፣ በጉጂ ዞኖች ውስጥ የሚፈፀሙ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን አስመልከቶ የሰላም፣ ፍትሕና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጥሪ አቅርቧል።

የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ( ካርድ ) ዳይሬክተር አቶ በፍቃዱ ሃይሉ፤በኦሮሚያ ክልል፣ጉጂ ዞኖች፣ለዓመታት የዘለቀ ነውጥ አዘል ግጭት በታጣቂዎች እና በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች መካከል ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም በሁለቱ መካከል በተካሄደው ግጭት ሳቢያ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እየደረሱ ቢሆንም ጉዳዩ ትኩረት ተነፍጎታል ብለዋል።
በዚህም ካርድ ላለፈው አንድ አመት ከመንፈቅ ፣ከተለያዩ የጉጂ ዞን ነዋሪዎች ጋር የምክክር መድረክ በማዘጋጀት በነውጥ አዘል ግጭቶች በንፁሃን ላይ የደረሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መረዳት ተችሏል ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈ አቶ በፍቃዱ ሃይሉ ከአከባቢው ለተውጣጡ ምሁራን፣የመብቶች ተሟጋቾችና ሌሎችም፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በመከታተል መሰነድና ሪፖርት ማድረግ የሚያስችል ስልጠና መሰጠቱን ገልፀዋል።

በመሆኑም በነዚህ አከባቢዎች እየተፈፀሙ ያሉ በደሎችን መረጃ ለብዙዎች ማድረስ እንዳልተቻለና የሚመለከተው አካልም መፍተሔ ሊሰጥ ባለመቻሉ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ አሰቃቂ ድርጊቶችን በመሰብሰብ የዳሰሳ ጥናት በዛሬው እለት ቀርቧል፡፡

በሪፖርቱ የተካተቱት 36ቱ ማሳያ ታሪኮች – በአማፂ ታጣቂዎችና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ ንፁኃን ላይ የተፈፀሙ ግድያዎች፣ የዘፈቀደና የጅምላ እስሮች፣ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ የንብረት ውድመት፣ አስገድዶ የመሰወርና የገንዘብ ማግኛ ድርጊቶች፣የማሰቃየትና ኢሰብዓዊ አያያዝ፣ እንዲሁም የማፈናቀል ድርጊት የተፈፀመባቸው ንፁኃን ዜጎችን ታሪኮችን የያዘ ነው።

የሪፖርቱ ዓላማ ጉጂን ማሳያ በማድረግ በተለያዩ የኢትዮጵያ አከባቢዎች የነውጥ አዘል ግጭቶች በሙሉ በተኩስ አቁም ተቋጭተው፣በፖለቲካ ድርድር እንዲፈቱና ዜጎች ሰላማዊ፣የተረጋጋ ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ውትወታ ለማድረግ ነው ተብሏል።

በመሆኑም ካርድ በነውጥ አዘል ግጭቶች የሚመጣ አዎንታዊ ለውጥ አለ ብሎ የማያምን በመሆኑ ፣ በነውጥ የሚሳተፉ አካላት በሙሉ በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደርሱ፣ ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት ሐቀኛ እና አሳታፊ ድርድሮች እንዲደረጉ፣ በነውጥ አዘል ግጭቶች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ፍትሕ እንዲያገኙ፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈፃሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ሲል ጥሪ አቅርቧል።

በልዑል ወልዴ

ሰኔ 08 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply