በኦሮሚያ ክልል እና በሲዳማ ክልል አዋሳኝ የድንበር ወረዳዎች ላይ ተቀስቅሶ በነበረው ግጭት በአጠቃላይ የስምንት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ጎዳት እንደደረሰባቸው ተረጋግጧል፡፡የሲዳማ ክ…

በኦሮሚያ ክልል እና በሲዳማ ክልል አዋሳኝ የድንበር ወረዳዎች ላይ ተቀስቅሶ በነበረው ግጭት በአጠቃላይ የስምንት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ጎዳት እንደደረሰባቸው ተረጋግጧል፡፡
የሲዳማ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ‹‹ ግጭት የተቀሰቀሰው በሲዳማ ክልል ፣ ጪሪ ወረዳ ፣ ሀሌላ ቀበሌ ነዋሪዎች ዘንድ ታዋቂ የሆኑ የሀገር ሽማግሌ መገደላቸውን ተከትሎ ነው ›› ብለዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም በስልክ ያናገራቸው የምዕራብ አርሲ ዞን የመስተዳዳር እና ጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ ኮማንደር ጌታቸው ታዬን ከዚህ በፊት ተመሳሳይ የድንበር እና የወሰን ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ግጭቶች እንደሚከሰቱ ተናግረው በዚህ ዓመት ግን ይህ የመጀመሪያው መሆኑን አንስተዋል፡፡

የወሰን እና የድንበር ጥያቄዎች ያሉባቸውን ስፍራዎች በመለየት ክልሎቹ እርስ በእርስ እንዲሁም እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድርስ በማድረስ እንዲፈቱ ብርቱ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት ችግሩ መከሰቱን ተናግረዋል ፡፡ የአሁኑ ግጭት ግን ከዚህ ጋር እንደማይገናኝ ገልጸዋል፡፡

ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች አንድ አባት ተገድለው መገኘታቸውን ተከትሎ በተነሳ ግጭት ከምዕራብ አርሲ ስድስት ሰዎች ሲገደሉ ዘጠኝ ያህል ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ኮማንደር ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በሰጡት መግለጫ እንዳሳወቁት በግጭቱ እስካሁን ከሲዳማ በኩል የሀገር ሽማግሌውን ጨምሮ ቢያንስ 2 ሰዎች ሲገደሉ ፤ ከቦናና በዳዬ ሆስፒታል በተገኘው መረጃ 15 ሰዎች በጥይት ቆስለዋል ።

የምዕራብ አርሲ ዞን የመስተዳዳር እና ጽጥታ ዘርፍ ሀላፊ ኮማንደር ጌታቸው ታዬ ችግሩ የተከሰተበት ስፍራ ራቅ ያለ በመሆኑ በእኛም በሲዳማ ክልልም በኩል መከላከያን ሰራዊት ይዘን በስፍራው ለመድረስ ከሁለት ሰአታት በላይ ፈጅቷል ፤ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰውም ለዚህ ነው በማለት ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ ገልጸዋል ፡፡

አካባቢው ላይ አሁን መከላከያን ጨምሮ የሁለቱም ክልሎች ልዩ ሀይል ፖሊሶች የማረጋጋት ስራ እየሰሩ ነው ፤ ጉዳዩንም ማጣራት ተጀምሯል ብለውናል ፡፡

መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም

የይኔአበባ ሻምበል

Source: Link to the Post

Leave a Reply