በኦሮሚያ ክልል ከ16 ሺሕ 800 በላይ የውሃ መሳቢያ ጄኔሬተሮች ለአርሶ አደሮች ሊከፋፈሉ ነው

በቢሾፍቱ ከተማ ጀብዱ ሞተርስ ያስገነባው የግብርና መሳሪያዎች ማምረቻ ፋብሪካ ተመርቋል

ማክሰኞ መስከረም 3 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት የገጠር ልማት ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችል ከ16 ሺሕ 800 በላይ የውሃ መሳቢያ ጄኔሬተሮችን ለአርሶ አደሮች ሊያከፋፍል መሆኑ ተገለጸ።

ጀብዱ ሞተርስ ያመረታቸውን የውሃ መሳቢያ ማሽኖች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተገኝተው መርቀዋል።

የክልሉ መንግስት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት፣ የአገሪቱን ኤክስፖርት ማሳደግ እና የሥራ እድል መፍጠር ላይ ትኩረት ሰጥቶ አየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው ጀብዱ ሞተርስ የገጣጠማቸው አነስተኛ እና መካከለኛ የውሃ መሳቢያዎች ለአርሶ አደሮች የሚከፋፈሉ ሲሆን እነዚህም የውሃ መሳቢያዎች ከ16 እስከ 44 ሊትር በሰከንድ መሳብ የሚችሉ መሆናቸው ተገልጿል።

አርሶ አደሮቹ በአምስት ዓመት ውስጥ በሚከፈል ብድር ማሽኖቹን መውሰድ የሚችሉ ሲሆን፤ የአንድ ዓመት የብድር እፎይታ እንደሚሰጣቸውም መነገሩን ዋልታ ዘግቧል፡፡

የማሽኖቹ ዋጋ የአርሶ አደሮቹን አቅም ያገናዘበ ሲሆን፤ የፋብሪካው ሥራ መጀመርም እንደ አገር ያለውን የውሃ መሳቢያ ማሽን እጥረት የሚቀርፍ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

እስከ 75 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችሉት ማሽኖቹ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply