በኦክላንድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በደረሰበት ጥቃት 3 ሰዎች በስለት ተወግተው መቁሰላቸውን ፖሊስ አስታወቀ

ማክሰኞ መስከረም 24 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በካሊፎርኒያ ግዛት ኦክላንድ ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በደረሰበት ጥቃት ሦስት ሰዎች በስለት ተወግተው መቁሰላቸውን የኦክላንድ ፖሊስ አስታውቋል።

ጥቃቱ የደረሰው በኦክላንድ አውራ ጎዳና 13 አቅራቢያ “ማውንቴን ቡሌቫርድ 4100 ብሎክ” ላይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መካነ ሰላም መድኃኔዓለም ካቴድራል ውስጥ ሲሆን፤ ጥቃቱ ከቀኑ 9 ሰዓት በኋላ መፈጸሙን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

የፖሊስ መኮንኖች ወደ ቤተክርስቲያኑ ሲደርሱ ከቀላል እስከ መካከለኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሦስት ሰዎች ማግኘታቸውን የኦክላንድ ፖሊስ ቃል አቀባይ ካንዳንስ ኬስ ተናግረዋል።

ሦስቱ ተጎጂዎች የኦክላንድ፣ የሳን ፍራንሲስኮ እና የሪችመንድ ነዋሪዎች መሆናቸውን ባለስልጣናቱ የተናገሩ ሲሆን፤ የተጎጂዎቹ ማንነት እስከአሁን አለመገለጹን ሳን ፍራንሲስኮ ክሮኒካል ዘግቧል።

የቤተክርስቲያኒቱ ምስክሮች ሦስቱን ተጎጂዎች በስለት ያቆሰለው ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉን የገለጹ ሲሆን፤ የኦክላንድ ፖሊስ ግለሰቡን “የሳን ፍራንሲስኮ ሰው ነው” ሲል ገልጾታል።

ኬስ ባለሥልጣናቱ ለችግሩ መንስኤ የሆነውን ነገር አሁንም እያጣሩ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ተጠርጣሪው የቤተክርስቲያኒቱ አባል ይሁን ወይንም ድርጊቱን በጥላቻ ተነሳስቶ የፈጸመው ወንጀል ነው የሚለው እየተመረመረ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

The post በኦክላንድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በደረሰበት ጥቃት 3 ሰዎች በስለት ተወግተው መቁሰላቸውን ፖሊስ አስታወቀ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply