በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት የመከላከያ ሰራዊት አባላት

አዲስ አበባ፣ግንቦት 23፣2014 ባለሀብቶችን በመሰለል፣ በማገት እና በማስፈራራት ገንዘብ በጠየቁ እና በተቀበሉ የመከላከያ ሚኒስቴር አባላትና ግብረአበሮቻቸው ላይ ክስ ተመሰረተ፡፡ ወንጀሉን ፈጽመዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው በመከላከያ ሚኒስቴር በ93ኛ እና 94ኛ እግረኛ ክፍለ ጦር አባል የሆኑት 1ኛ መቶ አለቃ ሀጂ ቱሉ߹ 2ኛ ኦፊሰር መንግስቱ በቀለ߹ 3ኛ ሻምበል ካህሊ መላክ߹ 4ኛ ሻለቃ ዱጉማ ዲምሳ ናቸው፡፡

በንግድ ስራ ተሰማርተው የሚገኙ 4 ግብረ-አበሮቻቸውም ክስ እንደተመሰረተባቸው ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የመከላከያ መኪና በመያዝ ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ሃብት ማስመለስ የመጣን ዐቃቤ ህጎች ነን ህገ ወጥ ዘይት߹ ስኳር እና የጦር መሳርያ ስለምትሸጡ በወንጀል ትፈለጋላችሁ በማለት 8
ነጥብ 5 ሚሊየን ብር መጠየቃቸው የክስ መዝገባቸው ያስረዳል፡፡

ተከሳሾቹ በቡድን በመደራጀት ባለሀብቶችን ኢላማ አድርገው ጥናት በማድረግ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው ተመልክቷል፡፡
በዚህም 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ታርጋ የለጠፈ የመከላከያ መኪና ይዘው ወደ ግል ተበዳይ ቤት በመሄድ በመኪና አግተው ከወሰዱት በኋላ 5 ሚሊዮን ብር ክፈል ካልከፈልክ ግን ልጆችህን ጭምር እንገላቸዋለን ብለው በማስፈራራት 710 ሺህ ብር ተቀብለዋል፡፡

5ኛ እና 7ኛ ተከሳሽ ደግሞ ሌላ ተበዳይን በመከላከያ እየተከታተሉ ስጋት እንዲገባው በማድረግ ጉዳዩን ለፖሊስ ቢያስረዳም የፖሊስ አዛዡን ጭምር ህጋዊ መስለው እደሚፈለግ በማሳመን እህቱን አስጠርተው ከያዟት በኋላ ወንድምሽ እንዲፈታ ከፈለግሽ 3 ሚሊዮን ብር ክፈይ እዳሏት ተገልጿል፡፡ በ3ኛ ክስ ቀኑ በውል ባልታወቀ በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም ደግሞ ወ/ሮ አዜብ በርሔ የተባለች ግለሰብን 5ኛ እና 7ኛ ተከሳሽ ባለቤትሽ ጄነራል ነው ትግራይ በመሄድ እያዋጋ ነው ስለቤትሽም
እያጣራን ነው በማለት አስፈራርተው 405 ሺህ ብር ተቀብለዋል፡፡

ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉት ተከሳሾች በትናንትናው ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን ችሎቱ ያልተያዙት 7ኛ እና 8ኛ ተከሳሾችን ፖሊስ አፈላልጎ አንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት በተከሰሱት ላይ የመጀመርያ የክስ መቃወሚያ ለመስማትና ባልተያዙ ላይ የፖሊስን ምላሽ ለመጠባበቅ ለግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply