
በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አከባቢዎች በተለይም በጋራ መኖሪያ አካባቢ ለጫኝና አውራጅ አካላት የሚከፈለው ገንዘብ እንዳማረራቸው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ሲገልፁ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
ታድያ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ይህንን ህብረተሰቡን ያማረረ ድርጊት ፈር ለማስያስዝ ደንብ በማውጣት ማፅደቁን አስታውቋል፡፡
በከተማዋ ይሰሩ የነበሩት ጫኝና አውራጆች ከዚህ ቀደም በስራ ዕድል ፈጠራ ስር የነበሩ ሲሆን፣ ከተደራጁበት ዓላማ ውጪ ህብረተሰቡን ከማማረርም ባለፈ ለሰላምና ፀጥታ ስጋት ሆነው መቆየታቸውን የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ተናግረዋል፡፡
ይህንን ለመቆጣጠርም ጫኝና አውራጆችን ከማደራጀት ጀምሮ፣ የመቆጣጠርና የመከታተል ስራ በሰላምና ፀጥታ ቢሮ ስር እንዲሆን መደረጉን አንስተዋል፡፡
በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የሚገኙትን ማህበራት የማፍረስ ስራ በመስራት ጫኝና አውራጆችን መልሶ የማደራጀት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የማድራጀቱ ስራ ከተጠናቀቀ በኃላ ደንብ የወጣላቸው መሆኑና በአዲስ አበባበ ፍትህ ቢሮ የፀደቀ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ሊዲያ፣ በደንቡ ዙሪያ በተከታታይ ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
በፍትህ ቢሮ የፀደቀው ደንብ ላይም የጫኝና አውራጅ ስልጣንና ሀላፊነት እንዲሁም ለእያንዳንዱ ዕቃ ለማውረድም ሆነ ለመጫን ተመን ወጥቶለት ቁርጥ ክፍያ እንዲከፈል እንደሚደረግም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ይህ ደንብ ወደ ተግባር በሚገባበት ወቅት አሁን ላይ በጫኝና አውራጅ ማህበራት እና በማህበረሰቡ መካከል ያለውን ችግር በዘላቂነት ሊያሥቀር የሚችል መሆኑን ሀላፊዋ ተናግረዋል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም
Source: Link to the Post