በካሚላት መህዲ ላይ አሲድ የደፋው ግለሰብ ከ30 በላይ ሴቶችን በማጭበርበር ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለጸ

ሐሙስ ሐምሌ 7 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ከ13 ዓመታት በፊት በካሚላት መህዲ ላይ አሲድ ደፍቶ የግድያ ሙከራ ወንጀል በመፈፀም የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በማረሚያ ለ12 ዓመታት ቆይቶ በምህረት የተፈታው ደምሰው ዘሪሁን የማነ፤ አሁን ደግሞ ከ30 በላይ ሴቶችን ገንዘብ በማጭበርበር ወንጀል ተከሶ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል።

ከ13 ዓመታት በፊት በፍቅረኛው ካሚላት መህዲ ላይ አሲድ በመድፋቱ በጥር 21 ቀን 2000 በተከሰሰበት የግድያ ሙከራ ወንጀል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሞት ቅጣት የተላለፈበት ደምሰው ዘሪሁን የማነ የተባለው ወይም ራሱን ሳምሶን እያለ የሚጠራው ተጠርጣሪ፤ በወቅቱ ቅጣቱ ወደ የዕድሜ ልክ እስራት ተሻሽሎለት ማረሚያ ቤት ቢወርድም 12 ዓመት ከ7 ወራት እንደታሰረ እስራቱን ሳይጨርስ በይቅርታ ተለቋል።

ተጠርጣሪው ውሎ ሳያድር በተለያዩ ወንጀሎች ተከሶ ድጋሚ ታስሮ ስለመለቀቁም የፌደራል ፖሊስ ምርመራ ያመለክታል።

ከዚያ በሗላም ተጠርጣሪው ከ30 በላይ ሴቶችን ገንዘብ በማጭበርበር ወንጀል ተከሶ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል።

ለአብነትም ነዋሪነቷን በአገረ ጀርመን አድርጋ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በኮንስትራክሽን ዘርፍ በኢንቨስትመንት በተሰማራችው መሐሪት ክፍሌ ላይ ከባድ የማታለል ወንጀል ስለመፈፀሙ ፖሊስ አስረዱቷል።

ተጠርጣሪው የግል ተበዳይዋን የዋህነት እንደ ዕድል በመጠቀም ጥሩ ሰው መስሎ ቀርቧት በንብረቶቿ ላይ ውክልና እንደሰጠችው፤ ከዚያም ውክልናውን ተጠቅሞ የግለሰቧን ንብረቶች በሙሉ እንደሸጠባት የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ያሳያል።

በተጠርጣሪው እንደታለለች ዘግይታ የተረዳችው የግል ተበዳይ መሐሪት ክፍሌ፤ ንብረቶቿን ስታፈላልግ ቆይታ በቡራዩ እና ቦሌ አካባቢ ስላገኘቻቸው በተጠርጣሪው ላይ ክስ ትመሰርታለች።

ይህን የተረዳው ተጠርጣሪም ሦስና በተባለች ሴት ከሳሽነት እና በራሱ ምስክርነት በግል ተበዳይ ላይ ሀሰተኛ ክስ አዘጋጅቶ በመመስረት ደብረብርሃን ተወስዳ እንድትታሰር ያደርግና ፍርድ ቤት ሳትቀርብ ተደራደሪ ተብላ ክሷን እንድታነሳ ትደረጋለች።

ከዚያም የግል ተበዳይ “በወንጀሉ የፀጥታ አካላት ከተሳተፉ ቀጣይ ዋስትናዬ ምንድነው?” በማለት በስጋት ወደ ጀርመን ተመልሳ እዚያ ሆና ለፌደራል ፖሊስ ክስ በመመስረቷ በአሁኑ ጊዜ ግለሰቡ ከግብረ አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ሥር ስለመዋሉ ፖሊስ ገልጿል።

ተጠርጣሪው በእስር ቤት እያለ እና ከዚያ ከወጣ በሗላም በርካታ ሴቶችን በማታለል በርካታ የማጭበርበር ወንጀሎችን መፈፀሙን የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ማስታወቁን ኢቢሲ ዘግቧል።

በዚህ ተጠርጣሪ የወንጀል ድርጊት በፍትህ ተቋማት የሚያገለግሉ ጥቂት ግለሰቦች በተባባሪነት ስለመሳተፋቸው የጠቀሰው ጠቅላይ መምሪያው፤ በአኹኑ ወቅት ግለሰቡ ከነግብረ አበሮቹ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራው እየተካሄደበት መሆኑን አስታውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply