በካቡል ትምህርት ቤት በአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ፍንዳታ 19 ሰዎች ተገደሉ

https://gdb.voanews.com/80470000-c0a8-0242-7f57-08daa2afa0d2_w800_h450.jpg

አፍጋኒስታን ካቡል በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት፣ በበርካታ ተማሪዎች በተሞላ ክፍል ውስጥ፣ ዛሬ ጧት በደረሰ ከባድ የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ፍንዳታ፣ 19 ተማሪዎች ሲገደሉ ሌሎች 27 መቁሰላቸው ተገለጸ፡፡ 

የዐይን እማኞች እና የፖሊስ ባለሥልጣናት አደጋው የደረሰው የሀዝራ ሺኣ እምነት ተከታይ ነዋሪዎች በሚበዙበት፣ በምዕራብ ዳሽ ባርቺ በተባለው አካባቢ በሚገኘው ካጅ የትምህርት ማዕከል ውስጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ጥቃቱን ያወገዙት የካቡል ፖሊስ አቀባይ ካሊድ ዛድራን የታሊባን ጸጥታ ኃይሎች በአካባቢው የደረሰውን አደጋ እየመረመሩ መሆኑን ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል፡፡

አደጋው በደረሰበት ወቅት በታሊባን መመሪያ መሰረት በመጋረጃ በተለየ ክፍል ውስጥ የነበሩ 400 የሚሆኑ ወንዶችና ልጃገረዶች የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ልምድድ እየወሰዱ እንደነበር  ከአደጋው የተረፉት ተማሪዎች ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የካጅ ትምህርት ማዕከል ለቪኦኤ እንደተናገሩት ግን በአደጋው የሞቱት 25 ተማሪዎች ሲሆኑ 35 የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸውን ተናግረዋል፡፡ ለጥቃቱ እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ የለም፡፡ 

በአፍጋኒስታን የዩናትድ ስቴትስ የዲፕሎማሲ መልዕክተኛ ጥቃቱን አውግዘዋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply