በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ከይዞታቸው እንዲነሱ የተደረጉ ነዋሪዎቹ ቅሬታቸውን ለአሀዱ አሰሙ፡፡

ባለቅሬታዎቹ በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 02 ጀሞ ሁለት ሸገር ማዘሪያ አካባቢ ነዋሪነታቸውን ያደረጉ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡

ከ1968 ጀምሮ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ተሰጥታቸው በህጋዊነት የሚኖሩ ሲሆን ሀምሌ 07 ቀን 2013 ዓ/ም የእርሻ መሬታችን ተቀምቶብናል ሀምሌ 24 ደግሞ ለሊት ወደ 70 የሚጠጉ ግለሰቦች መኖሪያችን እና የእርሻ ቦታችን በማጠር የመሬት ወረራ ፈፅውብናል ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዳለን ብናሳያቸውም መሬቱን ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ  ሰጥቶናል የሚል ምላሻ ከወራሪዎቹ ተሰጥቶናል ብለዋል፡፡

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማንም ሆነ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመሬት ማኔጅመንትን ብጠይቅም ከአቅማችን በላይ ነው ከሚል ምላሽ ውጪ የተሰጠን ነገር የለም ሲሉ ቅሬታቸውን ለአሐዱ አሰምተዋል፡፡

አሐዱም የነዋሪዎችን የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ተመልክቷል፡፡ የይዞታ ማረጋገጫ እያላቸው ለምን ለሁለተኛ ወገን ይዞታ ተላልፎ ተሰጠ ሲል የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ እና የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመሬት ማኔጅመንትን ጠይቋል፡፡

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ መሬት ማኔጅመንት ችግሩ መኖሩን ገልፆ ነዋሪዎቹ ከኮልፌ ቀራንዮ የይዞታ ማረጋገጫ የተሰጣቸው ህጋዊ ናቸው ብሏል፡፡

ይሁን እንጅ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፍቃድ ሰጥቷቸው ያደራጃቸው ወጣቶች ችግሩን እየፈጠሩ ሲሆን በተደጋጋሚ ሲያጥሩብን ስናፈርስ ቆይተን አሁን ከአቅማችን በላይ በመሆኑ በቀጣይ ከከተማ አስተዳደሩጋር በመወያየት መፍትሄ ለመስጠት እንሞክራለን ሲሉ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የመሬት ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ስማ እግዜሩ ተናግረዋል፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መሬት ማኔጅመንት ግን ስለጉዳዩ የቀረበልኝ ቅሬታም ሆነ የተፈጠረ ችግር ስለመኖሩ ክፍለ ከተማው መረጃ የለውም ሲሉ የክፍለ ከተማው መሬት ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንግስቱ በላይ ተናግረዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢ ነዋሪዎቹ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ ይዞታቸው ከወራሪዎች እንዲጠበቅላቸው ይጠይቃሉ፡፡

ቀን 29/11/2013

አሐዱ ራድዮ 94.3

Source: Link to the Post

Leave a Reply